ምርትና አገልግሎቶች በተቀመጠላቸው ደረጃና ጥራት እንዲቀርቡ ተቆጣጣሪ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ምርትና አገልግሎቶች በተቀመጠላቸው ደረጃና ጥራት እንዲቀርቡ ተቆጣጣሪ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል
ሐምሌ 5/2014 (ኢዜአ) ምርትና አገልግሎቶች በተቀመጠላቸው ደረጃና ጥራት መቅረባቸውን ለማረጋገጥ ተቆጣጣሪ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን አስገነዘቡ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስገዳጅ ደረጃ የወጣላቸውን ምርቶች እና አገልግሎቶች ከሚቆጣጠሩ አስፈጻሚ ተቋማት ጋር ተወያይቷል።
ውይይቱ በዋናነት ሚኒስቴሩ ከተቆጣጣሪ ተቋማት ጋር "የቴክኒካል ደንብ ስርዓት" ተፈጻሚነትን በጋራ በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ እንዳለው መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት የንግድና የግብይት ስርዓቱ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እየሰራ ነው።
በዚህም ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የልማት ተቋማትን አቅም በማጠናከር ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪ የተቆጣጣሪ አካላትን አቅም በማጎልበት የቁጥጥር ስርአቱን የማዘመን ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም እንዲሁ።
ምርትና አገልግሎቶች በተቀመጠላቸው ደረጃና ጥራት መቅረባቸውን ለማረጋገጥ የተቆጣጣሪ ተቋማት የቅንጅት ስራ መጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል።
የብሔራዊ የጥራት መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ቴክኒካል አማካሪ አቶ ግርማ ማሞ በበኩላቸው፤ የምርቶች ጥራት ጉድለት እንደሀገር የንግድ ሚዛን መዛባት እንደሚያስከትል አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች የምታገኘውን ገቢ ለማሻሻል የምርት ጥራት ማስጠበቅ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበትም ነው ያነሱት፡፡
ከዚህ አኳያ ተቆጣጣሪ አካላት ለንግድ ስርዓቱ እንቅፋት የሆኑ የጥራትና የደረጃ ጉዳዮችን በመፈተሽ ረገድ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በቀለ፤ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ተወዳዳሪ ለማድረግ የተቀባይ አገራትን ዝቅተኛ ደረጃ ሟሟላት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
ድርጅቶች ከተቋቋሙ እና ማምረት ከጀመሩ በኃላ ደረጃ የሚጠይቁበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ ኢንስቲቲዩቱ በቀጣይ የደረጃዎች ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ የፍተሻ እና የምርመራ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከ12 ሺህ በላይ ደረጃዎች እና ከ 300 በላይ አስገዳጅ የጥራት ደረጃዎች እንዳሉ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።