ትርምስምሱ ቀንድ እና ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
ትርምስምሱ ቀንድ እና ኢትዮጵያ
አየለ ያረጋል (ኢዜአ)
የአፍሪካ ቀንድ የዘመኑ ትርምስምስ ቀጣና ነው፤ የግርግር መንደር ነው፤ ስያሜው እንደተዋጊ ቀንዳም በሬ ከግብሩ የተሰጠው ይመስል፤ አካባበው የውጊያ ቀጣና ነው።
ኢትዮጵያን ከድህነት ማውጣት ላይ በማተኮር ዲፕሎማሲያችን የትኛው አገር የተሻለ ጥቅም ይሰጠኛል የሚለውን በሚገባ ማየት ይኖርበታል።
…
በታሪካዊ፣ ባሕላዊና ተፈጥሯዊ ክስተቶች የደመቀ ነው። በተመሳሳይ በተፈጥራዊና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች መልኩ የጎደፈ ነው። ጉራማይሌው ክፍለ አህጉር-አፍሪካ ቀንድ። ቀንዱ የጥንት ሰብዓ ዘሮች ቅሪት መገኛ ነው። በብዝኃ ባህል፣ ኃይማኖት፣ ማንነት ተቆራኝ ማኅረሰቦች ባለቤት ነው። በጥንተ ስልጣኔው ከሮማዊያን ስልጣኔ ጋር ይጣቀሳል። ይህ መንደር በሰው ልጆች የጭቆና፣ የቅኝ ግዛትና ባርነት ሁነቶች ታሪክ አብይ ጎዳና ነበር። የባህር ማዶ ተጓዦች፣ ወራሪያን፣ ነጋድራሶች፣ ሳይንቲስቶች መንደሩን እየታከኩ ሾልከዋል። በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች የአፍረካ ቀንድ ትልቅ ስትራቴጂካል ስፍራ ነበር።
ምሥራቅና ምዕራብ ክፍላተ ዓለም በማቆራኘቱ የዓለማችን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ መዘውር ነው። ከስዊዝ ቦይ መከፈት በኋላ የአውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ የሶስትዮች ማቆራኛ አንጓ ነው። የሜዲቴራኒያን ባህርንና ሕንድ ውቅያኖስ ማዕዶት ወይም መሿለኪያ የሆነችው ባብ-ኤል-መንደብ የባህር ወሽመጥን ከጉያው ወሽቋል። ባብ-ኤል-መንድብ ደግሞ ከጂቡቲ፣ ከኤርትራና ከየመን የሚዋሰን የዓለም የንግድ ፍሰት መሿለኪያ በር ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚሉት በየዓመቱ 30 ሺህ መርከቦች ይርመሰመሱበታል፤ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ በየቀኑ ያልፍበታል፤ በቀን አንድ ቢሊዮን ዶላር የንግድ እንቅስቃሴን ያስተናግዳል፡፡ በዚህም ከእስያ 59 በመቶ፣ ከአውሮፓ 21 በመቶ፣ ከአፍሪካ ደግሞ 16 በመቶ የንግድ ግብይቶች መተላለፊያ መስመር ነው፡፡ ምስጢሩ ደግሞ ቀይ ባህርንና የኤደን ሰላጤን ማስተሳሰሩ ነው፡፡ እናም ዓለም ዘወትር የሚገበያይበት የምንጊዜም ብቸኛ የንግድ አውታር ሆናል።
መንደሩ የመላ አፍሪካዊያን አገራት የጋርዮሽ ጉባዔ መምከሪያ ነው። ከሁሉም በላይ አፍሪካዊያን ከዘመናት ቅኝ ግዛት፣ ባርነት፣ ኢ-ርቱዕ ንግድ ልውውጥ ትግልና መስዕዋትነት በኋላ የአንድነታቸው፣ የወደፊት አብሮነት ተስፋቸው፣ የሰላምና ደህንነት ደጀንነት የመሰረቱት ተቋም (የዛሬው የአፍሪካ ሕብረት) ደጅ ነው-ከቅኝ ግዛት ቀንበር ባልተንበረከከችው ኢትዮጵያ። ቀንዱ የራሳቸው ልዩ አወንታዊና አሉታዊ መልኮች ያላቸው ከሰባት ያላነሱ አገራትን ያቀፈ ቀጣና ነው።
ከጥቃቅን እስከ ግዙፋን ብርቅዬ የዱር እንስሳት አምባ ነው። የዓለማችን ወንዞች አለቃ የሆነውን ዓባይ/ናይል ያመነጨ፣ የዓለማችንን ሁለተኛውን ጥልቅ ሐይቅ ታንጋኒካን ያፈለቀ፣ የአፍሪካን ሰማይ ጠቀስ ተራራ ኪሊማንጃሮን የገተረ፣ የታላቁ ስምጥ ሸለቆ ተፈጥሯዊ ገፀ በረከቶች የተቸረ … መልከ ብዙ ፀጋዎችን ያቀፈ አካባቢ ነው።
የአፍሪካ ቀንድ ሥነ-ምህዳራዊ ክሽፈትም ሌላው መገለጫው ነው። በድርቅ፣ በርሀብና በቸነፈር የተጎሳቆለ፣ በድህነትና ስደተኝነት ስሙ የገነነ ቀጣናም ነው። ተደጋጋሚ ድርቅና አካባቢያዊ መራቆት ሰለባ ሆኗል። ይህም ህዝቦች ለመፈናቀልና ፍልሰት ዳርጓል። አካባቢያዊ ስነ ምህዳር አለመጠበቅ ውስጣዊ የሕዝብ ፍልሰቱን አንሮታል። ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ጥሪዎች ማዕከል ነው። በከፍተኛ ውስጠ ፍልሰት እና ስደት የሰዎች ዝውውር የሚካሄድበት በመሆኑ ‘የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ ጥናት የስደት ታሪክ ነው’ አሰኝቶታል። እናም ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ተለዋዋጭ ዝናብ፣ ግጭት፣ አቅመ ቢስ ተቋማት፣ መሃይምነት፣ ስራ አጥነት፣ ድህነት፣ ደካማ ኢኮኖሚ … መገለጫው የሆነ ቀጣና ነው። ለዚህም ለውስጥና ለውጭ ዓለም አብይ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
በጥቅሉ የአፍሪካ ቀንድ የዘመኑ ትርምስምስ ቀጣና ነው፤ የግርግር መንደር ነው። ስያሜው እንደተዋጊ ቀንዳም በሬ ከግብሩ የተሰጠው ይመስል አካባበው የውጊያ ቀጣና ነው። የግጭት፣ የብጥብጥና የሰብዓዊ ቀውስ ማዕከል ነው። ዘመዱም ባዕዱም ቀጣናውን በመቆጣጠር ምኞትን ለማርካት ሩጫ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ስፍራው የዓለም የዐይን ብሌን ነውና!
የኅያላኑ ርኩቻ፣ የቀንዱ አገራት ሽኩቻ እና የችግሩ መፍቻ
ዓለም ላይ ሙሉ በኩልሄ ተፈጥሯዊ ጸጋ የተቸረ ምድር ባለመኖሩ አገራት ፀጋን ተጋርቶ፤ ምርትን ተገበያይቶ፣ የጎደለን ተሞላልቶ፣ ተጠቃቅሞ የማደግ፣ የህዝቦችን ኑሮ ማረጋገጥ የዲፕሎማሲ መርህ ተደርጎ ይወሰዳል። ዳሩ ጥቂቶች ሃያላን አዛዥ ናዛዥ ብዙሃኑ ደግሞ ምንዝር በሆነባት ዓለም ይህ መርህ ተጥሷል። በታሪክ አጋጣሚ የአገራት የኅይል ሚዛኑ በመዛባቱ የኅያላኑ ቡድን የዲፕሎማሲን መርህ ጥሶ ጣልቃ ገብነትና ጫና መፍጠርን መለያው አደርጓል። የአፍሪካ ቀንድ ደግሞ ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ይሆናል። በኅያላኑና በቀንዱ አገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲ አንዱ በስመ-አጋዥ፤ ሌላው በርጥባን ሸክም ተንፏቃቂ የአራጣ አበዳሪና ተበዳሪ ግንኙነት ሆኗል። አበዳሪው እየከበረ፤ ተበዳሪው እየቆረቆዘ የሚድህበት የተቃርኖ መንገድ። ይህም ርጥባን ተጠቅሞ አገሮችን አንገቱ ላይ ገመድ እንደተጠለቀለት ውሻ በራስ ርምጃ የማንቀሳቀስ የቅኝ ገዥዎች ገመድ ነው። በእርዳታ ሰበብ እንዳሻው ማሾር፣ አልሾርም ካለም የማሰሪያ ገመዱን ተጠቅሞ ማሽመድመድ፣ የአገራትን መንግስታት ማፈራረስ፣ አፈንጋጭ የሚሏቸውን መሪዎች ማስወገድ ገሃዳዊ ስልት ነው። እናም አፍሪካ ቀንድ ያላባራ ግጭት ይዘንባል፤ መንግስታት በየወቅቱ በኅይል ይፈናቀላሉ። የቀጣናው አገራት የዕጅ አዙርና ወክልና ጦርነት ሜዳ ሆነዋል።
ቀንዱ በስትራቴጂካዊ አቀማምጡ ተመራጭነቱ የሁሉም የጥቅም ማዕከል ሆኗል። ኃያላን አገራት ለቀጣናው ባላቸው ፍላጎት ባለፉት አስር ዓመታት የባህር ላይ ውንብድናን መከላከል በሚል አጀንዳ ከየፊናው ተጠራርተው ባህር ኃይላቸውን በቀጣናው አስፍረዋል። በርግጥም ቀጣናው ላይ ማንዣበቡ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ ዕድሜ ለሶማሊያ የባህር ወንበዴዎች ይሁንና “ውሻ በቀደደው ጅቡ ይገባል” እንዲሉ ውንብድናን በመከላከል ሰበብ የጂቡቲ ወደብ በኃያላኑ የጦር መርከቦች ተጥለቀለቀች፡፡ ዛሬ ላይ ከሰባት በላይ አገራት የጦር ሰፈሮችን በቀጣናው ገንብተዋል። ሁሉም ዓለም አቀፍ የጦር ኃይሎች በአፍሪካ ቀንድ ለመስፈር አሰፍስፈዋል፤ ከባህር ወደ የብስ እሽቅድምድም፡፡ በአሜሪካ የተጀመረው ከባሕር ወደ የብስ የተደረገው እሽቅድድም ሁሉንም ኅያላን አስከትሏል። በተለይም ቻይና በአካባቢውና በጥቅል አፍሪካ ውስጥ ያላት ጥልቅ እንቅስቃሴ አሜሪካና ተከታዮቿ የምዕራብ አገራትን እንቅልፍ ከነሳ ውሎ አድሯል።
ቀድሞውኑ ከኢኮኖሚያዊ ትስስር ባለፈ በውስጥ ፖለቲካ ጣልጋ የማትገባው ቻይና ከቀጣናው እንድትወጣ በምዕራባዊያን ኢ-ቀጥተኛ ግፊቶች ቢኖሩም በተቃራኒው መሰረቷን እያሰፋች መጥላች። ባሳለፍነው ወርኅ የካቲትም በቀጣናው ልዩ መልክተኛ መሾሟ፣ በቅርቡም የቻይና ምስራቅ አፍሪካ ጉባዔ መጀመሯ፣ በአገራት መካከል የሚስተዋሉ የሰላም ችግሮችን ለመሸምገል እና ለማደራድር ዝግጁ መሆኗን ስትገልጽ መደመጧ በርግጥም ቻይና በቀጣናው ያላትን ተዕጽኖ እያጎላች መምጣቷ፤ የቀድሞ ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎቷ ወደ ፖለቲካዊ መልኮች እየተለወጠ መምጣቱን ያሳያል የሚሉ አልጠፉም። በቅርቡ በአፍሪካ ቀንድ አገራት ሰላም፣ መልካም አስተዳደርና ልማት አጀንዳዎች ላይ ያተኮረ የቻይና እና የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ጉባዔ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደበት ወቅት የቻይና አፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሹ ቢንግ ቻይና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳር መረጋገጥ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸው ነበር። በቀጣናው ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳድር እንዲዘረጋ፣ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ፣ በቴክኖሎጂና ምርምር፣ በፕሮክከቶች ፋይናንስ ድጋፍ እና በድህነት ቅነሳ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም እንዲሁ፡፡ ቻይና በኢኮኖሚ ረገድ ዘላቂነት ያለው ቀጣናዊ ትስስርን ማጎልበት፣ ሽብርተኝነትን መከላከልና ኢንቨስትምንት እንዲስፋፋ፣ መሰረተ ልማቶች እንዲዘረጉና የቀጣናው አገራት በወጪ ንግዳቸው የነጻ ገበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደምታደርግ ገልዋል። ይህ የቻይና እና የቀንዱ አገራት ሁለንታናዊ ግንኙነት በጎ ሚና ቢኖረውም በእያንዳንዱ አገራት ውስጥ ጉዳይ ገብተው መፈትፈት ለለመዱ ምዕራባዊያን ግን ምቾት የሚነሳ ጉዳይ ነው።
ከጅቡቲ ባሻገር በአልሸባብ የምትታመሰው ሶማሊያ እና በኤርትራ የባህር ዳርቻዎች የጦር ሰፈር መገንባት የሚሹ ሃይሎችም አልጠፉም። የዓረቡ ዓለም አገራት ወደቀጣናው የሚያድርጉት ግብግብም ሌላው ብዙ መልኮች ያሉት የቀንዱ ገጽታ ነው። የየመን ጦርነት ምክንያት በማድረግ ወደሽኩቻ የገቡት የሰላጤው አገራት ከየመን ተሻግረው ወደ አፍሪካ ቀንድ የጦር ሰፈር መገንባት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በየመን የሚገኙ ዓማፅያንን ለመዋጋት በሚል ሽፋን ምስራቅ አፍሪካዊቷን አገር እንደ ቁሳቁስ ግምጃ ቤትነትና መሸጋገሪያ ድልድይ በመጠቀም በቀጣናው የበላይነትን ለመጎናጸፍ የሚደረግ እሽቅድምድም እንደሆነ ተንታኞች ይገልጻሉ።
በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ ለሁሉም አካል የጥቅም ማዕከል ሆኗልና መልኩ ኢ-ተገማችች እና ተለዋዋጭ ነው። የብዙ ወገኖች እጆች ስለሚያተራምሱት ከአፍጋኒስታንና ከመካከለኛው ምሥራቅ ቀጥሎም ሶስተኛው መረጋጋት የተሳነው ቀጣና ሆናል። የኅያላኑ ርኩቻና ፍጥጫ ለቀንዱ አገራት ከተስፋ ይልቅ ለዘላቂ ሕልውና ችግር ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል። ቀንዱ በዓለም ላይ ከሚገኙ ቁልፍ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ወይም ጆኦ-ፖለቲካል አካባቢዎች አንዱ ቢሆንም የቀንዱ አገራት እርስ በርስ እየተናኮሩ፣ መንግስታትም ቀስ በቀስ እየከሸፉ መጥተዋል። የቀንዱ አገራት ያላባራ መልከ ብዙ ግጭትና ጦርነት ቁልፉ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።
የቀንዱን መልከ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ የቀንዱ አገራት ትብብር አይነተኛ መፍትሔ ነው። ቀንዱ በተፈጠሮ የመክበር ጸጋዎች ቢቸረውም ዕድሉን አልተጠቀመም፤ እንዳይጠቀምም ሳንካዎች በርክተዋል። እናም ሰላምና ጸጥታን ማረጋገጥ፣ ልማትና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያሻዋል። ለዚህ ደግሞ የልማት ተግዳሮቶችን በጋራ መጋፈጥ ይፈልጋል።
የቀንዱ አገራት ቀዳሚ ፈተና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ሚሊዮኖችን እየፈተነ ያለው ድርቅና ጎርፍ ነው። የሥነ ምህዳራዊ ክሽፈት ለተደጋጋሚ ድርቅና አካባቢያዊ መራቆት ሰለባ አድርጎታል። በአፍሪካ ቀንድ የድርቅ ተጋላጭ ማኅበረሰብ ቁጥር አሻቅቧል። በጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር 2011 በቀጣናው 16 ሚሊየን ዜጎች ለከፋ ጉዳት ተዳርገው ነበር። በጎርጎሬሳዉያኑ የዘመን ቀመር ታህሳስ 2021 ይፋ በሆነ መረጃ በሶማሊያ ብቻ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ ተጠቅተው ነበር። ቀደም ብሎም በሶማሊያ በተከሰተው ርሃብ ከሩብ ሚሊየን በላይ ሰዎች ሞተዋል። ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሶማሊያውያን ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት ገጥሟቸዋል። ባሳለፍነው ዓመት በኢትዮጵያ ከ40 ዓመታት ወዲህ እጅግ አስከፊ የተባለ ደርቅ ተከስቶ ነበር። ሶማሌ ክልልን የነካካው አስከፊ ድርቅ በሚሊዮን የሚቀጠሩ የቁም እንስሳትን ፈጅቷል፤ ኬኒያ እና ሱዳን በከፍተኛ ጎርፍ ተመተው የድረሱልኝ ጥሪ ማሰማታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
የሰሐራ በርሃማነት መስፋፋትና የስነ ምህዳር ክሽፈት ሌላው ፈተና ነው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና የሰሃራ በረሃ እየሰፋ የሳህል አገራትን አዳርሶ ለአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ስጋት መደቀኑን ያነሳሉ። የአየር ንብረት መዛባትን መቀነስ እንጂ ሙሉ በሙሉ ማስቆም እንደማይቻል ገልጸው፤ በዚህም የውሃ እጥረትን ጨምሮ መልከ-ብዙ ጉዳቶች ሊከተሉ እንደሚችሉ ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ እንደ ቀጣናው አባል ፈተናዎችና ስጋቶች እንዳሉባት በመረዳት በውሃ አጠቃቀም፣ በግብርናና መሰል ከአየር ንብረት መዛባት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ መቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች ይጠይቃል ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ በአየር ንብረት ለውጥ የሚጠበቅበትን እየሰራ እንዳልሆነ ይተቻሉ። በዚህም በርካታ የምርምር ተቋማትን በማቋቋም በጉዳዩ ላይ በስፋት ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመዋል። የቀጣናው ጥናትና ምርምር ተቋማትም ቢሆኑ በአፍሪካ ቀንድ እየተስፋፋ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት መቋቋም የሚያስችሉ የመፍትሔ አማራጮችን ማፍለቅ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በቅርቡ በተደረገው የቻይና ምስራቅ አፍሪካ የሰላምና የልማት ጉባዔው ላይ ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በውጭ ጣልቃገብነት፣ ግጭት፣ ድርቅና የዓለም አቀፍ ሁነቶች ሳቢያ የቀጣናው ህዝብ ለመልከ-ብዙ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መዳረጉን ጠቁመው ነበር። የቀጣናው አገራት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በመፍታት የቀጣናውን መጻኢ መዳረሻ መወሰን ይገባናልም ብለዋል። የቀጣናው አገራት በውጭ ኅይሎች ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለችግሮቻቸው በጋራ ሊመክሩ እና የመፍትሔ አካል መሆን እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት። ለቀጣናውን መዳረሻ መወሰን በአገራቱ እጅ ላይ የወደቀ መሆኑን ገልጸው፤ ለተፈጻሚነቱ ቁርጠኛ ሆኖ መስራት እንደሚገባና የቀንዱ ህዝቦች በቋንቋ፣ ሃይማኖትና በባህል የሚጋሯቸውን እሴቶች በመጠቀም በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ስትራቴጂካዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢጋድና አፍሪካ ሕብረት
የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን መጋፈጥ የሚቻለው ጠንካራ የጋራ ተቋማት በመመስረት መሆኑ እሙን ነው። ምስራቅ አፍሪካ በተለይ የአፍሪካ ቀንድ ተደጋጋሚ ድርቅ እና በጦርነት ያልተለየው ክፍለ አህጉር ነውና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን/ኢጋድ እና የአፍሪካ ሕብረት ለጉዳዩ መፍትሔ አይነተኛ ባለቤት መሆናቸው ይታወቃል። ነገር ግን ተቋማቱ ከሚጠበቅባቸው አኳያ ሚናቸውን በአግባቡ ለመወጣት አልቻሉም በሚል የሰላ ትችት ይቀርብባቸዋል።
ኢጋድ ድርቅን በጋራ መከላከል እና የጋራ ስትራቴጂ እየነደፉ ለልማት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የተቋቋመ ድርጅት ነው። በአውሮፓዊያኑ 1986 ‘የምስራቅ አፍሪካ የልማት እና የድርቅ መከላከል በይነ ድርጅት’ ሆኖ መቀመጫው ጅቡቲ አድርጎ ነበር የተመሰረተው። በ1996 (ከ10 ዓመታት በኋላ) የዛሬውን ስያሜ ይዞ ተቋቋመ። ትኩረቱንም ድርቅ ላይ ብቻ ሳይሆን የክፍለ አህጉሩ ሰላም፤ መረጋጋት እና ልማት ላይ አደረገ። ዛሬ ላይ ከ300 ሚሊየን ያላነሰ ህዝብ (የአፍሪካን ህዝብ ብዛት 20 ከመቶ በላይ) ያላቸው ስምንት አባል አገራት አቅፏል።
ኢጋድ ከተመሰረተ ሶስት አስርት ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም በቀንዱ አገራት ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማት ረገድ ምን ተጨባጭ ለውጥ አመጣ የሚለው ለብዙዎቹ አጠቃያቂ ሆኗል። በሌላ ጎኑ የኢጋድ ሚና ባይታከልበት ኖሮ የቀንዱ ችግር ከዚህም በላይ ይወሳሰብ ነበር የሚሉ ወገኖችም አልጠፉም። በአኗኗር ዘይቤና የምጣኔ ሀብት መሰረታቸው ተመሳስሎሽ ያላችውን የምስራቅ አፍሪካ አገራትን ወደ ብልፅግና የማሻገር ህልም ቢሰንቅም በአገራቱ መካከል ግጭት እና የፖለቲካ ዥዋዥዌ እንጂ ቀጣናዊ ትብብር እምብዛም አልዳበረም። ኢጋድ ለቀይ ባህር እና ለኤደን ባህር ሰላጤ ልዩ ትኩረት ሳይሰጥ በውስጥ ጉዳዩ ላይ ብቻ ማተኮሩም፤ ቀጣናው በኅያላን ሽኩቻ እንዲታመስ አድርጓል ትበሎም ይተቻል።
የኢጋድ አገራት ለጋራ ችግሮቻቸው የጋራ የድርጊት መርሐ ግብር ቀርጸው እንዲራመዱ ማስቻል የባለስልጣኑ ኅላፊነት ነው። በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለውን የኅያላን አገራት እሽቅድድም መልክ እንዲይዝ አገራቱን ወክሎ የመንቀሳቀስ፣ ቀንዱ የየጋረጠበትን የሥነ ምህዳር መቃወስ የማስተካከልና በድርቅና ታያየዥ ችግሮች የምግብ ዋሰትና ችግር ላለበት ቀጣና የምፍትሄ አማራጭ እንዲፈልቅ ማድረግ ስራ ይጠይቀዋል። በአገራቱ መካከል የሚስተዋል የጥርጣሬ ፖለቲካ፣ የዕጅ አዙር ጦርነቶች እና ግጭቶች መንስኤዎች፣ የድንበር ላይ ግጭቶች፣ የባህር ዳርቻዎች ይገባኛል ፍላጎቶች እና ርኩቻዎች ለኢጋድ የቤት ስራዎች ናቸው።
ከሰሞኑም በኬኒያ ናይሮቢ የተደረገው 39ኛው የኢጋድ መሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ ድርቅ፣ ጦርነት፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ ፖለቲካዊ ለውጦች፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ላይ ያተኮረ ነበር። በጉባዔው ማጠቃለያ በወጣው የጋራ የአቋም መግለጫ በኢጋድ አባል ሀገራትና በቀጣናው ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ የሚገኙ ውስጣዊና ውጫዊ የፖለቲካና የደህንነት ችግርችንም በጋራ መቋቋምና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ስራ መስራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥቷል። የሶማሊያ ምርጫን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አድንቋል፤ በሱዳን፣ በሰሜን ኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ችግሮች በሰላማዊ አማራጭ እንዲፈቱ ኢጋድ ሚናውን እንደሚወጣ ገልጿል።
በድርቅና የተፈጥሮ አደጋዎች የወደቀውን የምግብ ዋስትና ችግር ዘላቂ መፍትሔዎችን በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቁሟል። ዓለም አቀፍ አጋሮችና የረድኤት ተቋማት ሰብዓዊ ድጋፋቸውን አጠናክርው እንዲቀጥሉ በመሪዎች ጉባኤ ጥሪ ቀርቧል። የኢጋድ መሪዎች መግለጫ ግን እንደወትሮው ሰላምንና ልማትን ከመመኘት በስተተቀር ምኞትን እንዴት ማሳካት ይቻላል፤ የቀንዱን ፈተናዎች እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ግልጽ ነገር አልተንጸባረቀም።
ሌላው የአፍሪካዊያን ተቋም በዚሁ ቀጣና በአዲስ አበባ የሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት ነው። መላ አፍሪካዊያንን በአባልነት ያቀፈው ይህ ተቋም ግን የአህጉረቷን ብልጽግፍና ከማረጋገጥና ሰላምና ጸጥታን ከማስፈን አኳያ አቅመ ቢስ እንደሆነ ይተቻል። ሃያላን መንግስታት የአፍሪካን ሰላምና ጸጥታ በራሳቸው ሃዲድ ለማሾር ተግባራቸውን በብርቱ ቀጥለውበታል። የአፍሪካ ደህንነት ሁኔታ በፍጥነት ተለዋዋጭ ቢሆንም ሕብረቱ በየወቅቱ በሚፈነዱና አህጉራዊ የደህንነት ስጋት በሚፈጥሩ አዳዲስ ኅይላት ተጽዕኖ ፀጥታውን የመቆጣጠር ተስፋው የለመለመ አልሆን ብሏል። በአንድ ወቅት ለ‘ኒው አፍሪካን’ መጽሔት ዕይታቸውን የለገሱት ኢትዮጵያዊው ፕሮፈሰር መድህኔ ታደሰ (በሕብረቱ የቀድሞ የደህንነት አማካሪ) ከምዕራባዊያኑ ይልቅ ሕብረቱ ቀይ ባህር በጦር ሰፈሮች ሲጥለቀለቅ ፓሊሲ አለማውጣቱና በጉዳዩ ላይም አንዲትም ቀን ተሰብስቦ ባለመምከሩ ተችተው ነበር። የሰላጤው አገራት ቀይ ባህርን ሲቀራመቱት ትንፍሽ እንዳላለም ገልጸዋል።
እናም ሕብረቱ አህጉራዊ ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ትልሙን ስቷል ሲሉ ተችተዋል። ይልቁኑም ከሕብረቱ አፍንጫ ስር ነው የደህንነት ችግሮች ሲቀያየሩ የሚስተዋሉት ብለዋል። ቀጣናዊ የጸጥታ ጉዳዮች አፀፋ የሚሰጥ ተጠባባቂ የሰላም አስከባሪ ኅይልም እንደተዳከመ ይገልጻሉ። በሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ መሪነት ሕብረቱ በፋይናንስ ራሱን ችሎ እንዲቆም የማድረግ ዕቅድ ለአፍሪካ መልካም ጅምር ቢሆንም ጠንካራ አህጉራዊ አመራር ባለመሰጠቱ ግቡን አልመታም። የወቅቱ ዓለም አቀፋዊ የደህንነት አደረጃጀት ለአፍሪካ ስጋት ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት፤ የአፍሪካን ሰላምና ደህንነት አጀንዳ ባለቤት የመሆን ጉዳይ መሪዎች ሊያስቡብት እንደሚገባ መክረዋል። በአህጉሪቷ የግጭት መንስኤ የሚያጠኑ ጠንካራ ተቋማት እንደሚያስፈልጉም እንዲሁ። የአፍሪካ መሪዎች በማህበረሰባቸው ውስጥ የፖለቲካን መነጣጠል የማጥበብ፣ አካታች ፖለቲካዊ ሂደትን የመዘርጋትና የዲሞከራሲ ምህዳርን የማስፋት ከአፍሪካ አገራት መሪዎች ይጠበቃል። እነዚህ አህጉራዊ ፖለቲካዊ ቁልፍ ጉዳዮች ዕልባት ካልተበጀላቸው የ2063 የአህጉራዊ መዋቅራዊ ሽግግር አጀንዳ ማሳካት ከባድ ነው።
አጀንዳ 2063 ሰላማዊት፣ የበለጸገችና ያደገች አፍሪካን ለመገንባት ሃሳብ የሰነቀ ግብ ነው። ይህን አህጉራዊ ግብ ማሳካት የሚቻለው ታዲያ ሁሉም አገር በየቤቱ ያለውን አካባቢ ሰላም ሲያረጋግጥ እንደሆነ ባለሙያዎች ያምናሉ። ካልሆነ ግን አንዱ ደፍርሶ የሌላው ጎረቤት አገር ሰላምና ፀጥታ አይረጋገጥም። ለአህጉራዊ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እና ሁለንተናዊ ዕድገት ዋስትና ግጭቶች ባሉበት አካባቢ የሰላም ተጠባባቂ ኅይል ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ፣ ቀንዱ እና የይሁንታ ጥቁምታዎች
የአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል በተለይ ኢትዮጵያ ላይ ልዩ ትኩረት ይደረጋል። በቀጣናው ያሰፈሰፉ ኅያላንም ሆነ ለኅያላኑ በትሮይ ፈረስነት የሚያገለግሉ መንግስታት ለየራሳቸው ጥቅም ሲሉ ኢትዮጵያን ይነክሳሉ። ይህም የዛሬና የወደፊት ስጋት ሳይሆን የትናንትም ታሪክ ነው። ኢትዮጵያ በተለይም በምዕራባዊያን ዘንድ የተቄመባት አገር ናትና። ኢትዮጵያ ከዓለም ሃያላን ጥርስ ውስጥ የገባች በዲፕሎማሲው መስክ የምዕራቡ ዓለም እንዳሻው ሊጫወትባት የሚሻት አገር ነች። በርጥባን ከሚሞከር ዲፕሎማሲያዊ ጫና ባሻገር ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጠረው ጫና እና የጣልቃገብነት ግብግብ አንድምታ መልከ ብዙ ነው።
ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በዲፕሎማሲው መስክ ኢትዮጵያን ያገለገሉት አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና በአንድ ወቅት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ምዕራባዊያን በየዘመኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና አመክንዮ በዋናነት ከአድዋ ድል ጋር ያያይዙታል። ይኸውም በአውሮፓዊያኑ 1884 የበርሊን አፍሪካን የመቀራመት ጉባዔ በኋላ ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛትን ድል አድርጋ የአፍሪካዊያን የነጻነት ትዕምርት መሆኗ በክፉ ዓይናቸው እንዲመለከቷት ሰበብ መሆኑ ነው። ድሕረ አድዋ ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት ሆና መቀጠሏ፤ የጥቁር አፍሪካዊያን ታሪክና ስልጣኔ ቅርስ መሆኗም ለነጮች መጥፎ ስሜት እንዲያድርባቸው አድርጓል ባይ ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ደካማ በመሆኗ ከምዕራባዊያን ጋር ግንኙነት ቢኖሯትም ዳሩ ችግር በገጠማት ወቅት አንድም ጊዜ ከጎኗ አልተሰለፉም፤ በተቃራኒዋ ቆመዋል እንጂ ይላሉ አምባሳደር ጥሩነህ።
ለአብነትም የ1928ቱን የፋሺስት ኢጣሊያ የግፍ ወረራ የመንግስታቱ ማኅበር ማስቆም አለመቻሉ፣ የራሷ ጦር መሳሪያ ከምታመርተው ኢጣሊያ ጋር እኩል ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ መጣላቸው ብሎም በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መንገድ መሳሪያ እንዳታጓጉዝ መከልከላቸውን ይጠቅሳሉ። በሶማሊያ ወረራ ወቅትም ለኢትዮጵያ ወዳጅ አገር የምትባለዋ አሜሪካ የግፍ ወረራ ሲፈጸም ክፍያ የፈጸመችበትን የጦር መሳሪያ ከመከልከል ባለፈ ከታሪካዊ ጠላቶች በመወገን ኢትዮጵያን መክዳቷን ያወሳሉ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እና ለቀይ ባሕር ስትራቴጂክ ስፍራ ያላት መልክዓ ምድራዊ አቀማምጥ ለምዕራባዊያን ስጋት ትሆናለች በሚል እንድትዳከምና እንድትፈራርስ የምንጊዜም ፍላጎታቸው ነው ይላሉ። እነዚህ ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ወደ ገደል ሲገፏት የነበሩ ምዕራባዊያን ዛሬም በገጠማት የሕልውና አደጋ አሜሪካን ጨምሮ ከአሸባሪው ቡድን ጋር መወገናቸው ህወሓትን ወደውት ሳይሆን ኢትዮጵያን ለመበታተን ሊጠቀሙበት ስለፈለጉ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በቀጣናው የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶች፣ የሽብርተኛ ድርጅቶች እንቅስቃሴዎች፣ የአገሮቹ ተለዋዋጭ አሰላለፎችና ተቃርኖ መልካቸውን መለዋወጥ ለኢትዮጵያ ትልቅ አንድምታ አለው። የታሪክ ምሁሩ ዶክተር አደም ካሚል (ረዳት ፕሮፌሰር) ምዕራባዊያንና የአረብ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ዘመን ተሻጋሪ ጫናዎች የየራሳቸው መንስኤ እንዳላቸው ይገልጻሉ። ግብጽ በተለይም የዓረቡን ዓለም በአባይ ፖለቲካ ጉዳይ ከጥንት እስክ ዛሬ በሀሰተኛ ትርክት በማሳመን አትዮጵያን ለማዳከም ያልፈነቀለቸው ደንጋይ እንደሌለ ለአብነት ያነሳሉ።
የዓባይ ፖለቲካ ዛሬም ዋነኛ የጠላት አጀንዳ እንደሆነ ገልጸው፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል ብሎም የወደፊት በአባይ ወንዝ ላይ አሳሪ ውሎችን ለማስቀመጥ በየጊዜው ያልተቋረጡ አጅንዳዎችን እንደምታመጣ ያነሳሉ። አሁን ላይ የግብጽና መሰሎቿ አጀንዳ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ውላችው አስረው መያዝ እንዳልቻሉ ሲረደዱ ሁነኛ አጀንዳቸው ውስጣዊ ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር፣ ክልሎችን ገነጣጠሎ ወደ ጎረቤት አገራት መለጠፍ አጀንዳ በምሁራኖቻቸው በኩል እያስተጋቡ እንደሆነ ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ውስጠ ጉዳይ በሃይማኖትም ሆነ በፖለቲካ ልዩነት አጥር ሳይበጅ አንድነትና ብልጠት እንደ እንደሚያስፈልግ እና መንግስትም አገርን ማዳን ላይ በትኩርት ሊሰራ እንደሚገባው ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ በእስልምናው ዓለም ትልቅ ከበሬታ እንዳላት፣ በአፍሪካ አገራትም ዘንድ በነጻነት ቀንዲልነቷ ከፊት የምትቀድም አገር እንደሆነች ገልፀው፤ ይህን አጋጣሚ በዲፕሎማሲው መስክ መጠቀም እንደሚገባ ይናገራሉ። ከጎረቤቶቿም ሆነ ከአጠቃላይ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር ያሻታል። ከጅቡቲ፣ ሶማሊያና ኬንያ ጋር ያለው ምጣነ ሀብታዊ ግንኙነት ማጠናከር፣ ከአባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋርም ሰላም፣ ዕድገትና ብልጽግና ባረጋገጠ እንዲመራ ይመከራል። በሌላ በኩል በአንዳንድ ጎረቤት አገራት በኩል ያለው ግንኙነትም ሊጤን ይገባል ይላሉ። ለአብነትም ሱዳንን ያነሳሉ። በየጊዜው የሚመጡ መሪዎች ከሱዳን ህዝብ ፍላጎት ውጭ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽሙት ደባ በኢትዮጵያ በኩል በጥልቅ ሊታሰብበት እንሚገባ ገልጸዋል። ኢትዮጵያና ሱዳን እንደ ህዝብ በመልክ፣ በቋንቋ፣ በባህል ተመሳስሎሽ ያላቸው፣ ከ1 ሺህ 600 በላይ ኪሎሜትር ድንበር የሚጋሩ አገሮች እንደሆኑ ይገልጻሉ። በታሪክ አጋጣሚ ግን የሱዳን መሪዎች በርካታ ደባዎች መፈጸማቸውን ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ የቀድሚ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የዛሬው አፍሪካ ሕብረትን) ደግሳ መስርታለች፤ በራሷ ከተማ ጎጆ አውጥታለች። አፍሪካዊያን በፓን አፍሪካዊነት መንፈስ በማሰባሰብ ከባርነት ቀንበር ነጻ እንዲወጡ የመሪነት ሚናዋን ተወጥታለች። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት እንዲመሰረት ሚናዋ ጉልህ ነው። ሁልጊዜም ከሩቅም ከቅርብም ወረራና ሴራ ብታስተናግድም ኢትዮጵያ ቀድሞውኑም ከጎረቤቶቿ ጋር በቅርበት እና በእኩል ተጠቃሚነት ለመስራት ለፍታለች። ኢትዮጵያ ይህን የቀደመ አገራትን የማስተባበር፣ ተቋማንትን የመገንባትና ተዕጽኖዋን የማጎልበት ሚናዋን ልትወጣ ይገባል።
ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ መቆየቷ ብቻ ሳይሆን ለህዝቦች ነጻነት፣ ሰላምና መረጋጋት በበርካታ አገሮች በተጫወተችው ሚናም ለአፍሪካ ህብረትና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ማዕከል መሆን አስችሏታል፡፡ ከፖለቲካ ማዕከላዊነቷ ባሻገር የገጠማትን ውስጣዊ የህልውና ፈተናዎች ተቋቁማ የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን ማረጋገጥ ይገባታል። ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የቱንም ያህል ተለዋዋጭ ተለዋዋጭ ዲፕሎማሲ ይጠይቃል።
ኢትዮጵያ የባሕረ ሰላጤው ወይም ሌሎች የዓረብ ሊግ አገሮች የማይተኙላት ታሪካዊ ጠላቶች አድርጋ ባትመለከትም ተለዋዋጭ ክስተቶችን እንዳመጣጣቸው በመገምገም ነባራዊውን ሁኔታ ያገናዘበ ስልት ወይም ስትራቴጂያዊ ርምጃ በመውሰድ ብሔራዊ ጥቅሟን የማስጠበቅ ፖሊሲ መከተል እንደሚገባት ምሁራን ይናገራሉ። እንደ ሌሎች አገሮች በቦታው በመገኘት አለያም በሌላ መልኩ ስትራቴጂካዊ ስልቶችን ቀይሶ በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅባትም እንዲሁ፡፡
በዲፕሎማሲ ቋንቋ ዘላቂ ወዳጅና ጠላት የለም። የዲፕሎማሲ መርህ ብሔራዊ ጥቅም ነው፤ የሉዓላዊነት ክብር ነው። አምባሳደር ጥሩነህ አንዳንድ ምዕራባዊያን ከትናንት እስከ ዛሬ ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲሰሩ እንደቆዩት ሁሉ ነገም ምቹ ጊዜ እየጠበቁ ኢትዮጵያን ለመበታተን ከመሞከር አይቦዝኑም ይላሉ። ለዚህ መፍትሄው ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል የመገንባት፣ ውስጣዊ አገራዊ ስሜት የመፍጠር እና የኢኮኖሚ አቅምን የማጠናከር እርምጃዎች እንዲወሰዱ ይመክራሉ። በኢኮኖሚ ረገድም ቢያንስ የምግብ ፍጆታ በአገር ውስጥ ምርት መሸፈን እንዲሁም የግብርና መሳሪያዎች ከሺህ ዘመናት ከነበረው ኋላቀር ስርዓት መላቀቅ እንዳለባቸው መክረዋል። የኢኮኖሚ ጥገኝነት እያለ የፖለቲካ ነጻነትን ማረጋገጥ ስለማይቻል ከግብርና ግብዓቶች ግዥ እና ከልመና መውጣት ያሻል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕልውና ተጠብቆ እንዲቀይ ብሔራዊ ስሜትና ውስጣዊ አንድነትን የሚያጠናክር የትውልድ ግንባታ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ኢትዮጵያን ከድህነት ማውጣት ላይ በማተኮር ዲፕሎማሲያችን የትኛው አገር የተሻለ ጥቅም ይሰጠኛል የሚለው መታየት ይኖርበታልም ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በየዘመናቱ የተፈተነ በመጥፎ ጊዜ እንድ ሆኖ የተሻገረ፣ ፋሽዝምን ያለፈ ጠንካራ ህዝብ በመሆኑ አሁንም በድል ይወጣዋል ብለዋል።