የተለያዩ ተቋማት በጋራ በመተባበር በአንድ ቀን ከ10 ሺህ በላይ ችግኞችን ተከሉ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ተቋማት በጋራ በመተባበር በአንድ ቀን ከ10 ሺህ በላይ ችግኞችን ተከሉ
ሐምሌ 5/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከሚዲያ፣ ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪና የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በአንድ ቀን ከ10 ሺህ በላይ ችግኞችን ተከሉ።
ድርጅቱ አራተኛውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በኦሮሚያ ክልል ሉሜ ወረዳ የጠዴ ዲልዲማ ቀበሌ ገበሬ ማህበር አከናውኗል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሮባ መገርሳ፤ በአካባቢው ቦታ በመረከብና በማልማት ጥብቅ ደን እንዲኖር ድርጅቱ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአካባቢው የተሰጠውን ቦታ በማጠር ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ ለችግኞች እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ድርጅቱ እስካሁን ከ45 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል ወጣቶችን ቀጥሮ እንክብካቤ በማድረግ አካባቢውን የማልማት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በድርጅቱ የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ዳይሬክተር ደረጄ ሚደቅሳ፤ ከአካባቢው 17 ሄክታር መሬት በመረከብ የችግኝ ተከላና ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
እስካሁን ከተተከሉት ከ80 በመቶ በላይ ችግኞች መጽደቃቸውን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ የሚተከሉትንም የመንከባከብ ሂደቱ ይቀጥላል ብለዋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ ከተሳተፉት ተቋማት መካከል የፌዴራል ፖሊስና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ይገኙበታል።
በፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የኮንትሮባንድ ድንበርና ትራንስፖርት መምሪያ የተሳተፉት ረዳት ኮሚሽነር አንሻ ቶላ፤ ሰራዊቱ ከወንጀል መከላከል በተጓዳኝ በልማት ሥራዎች ላይ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው እለት በአዳማና ሞጆ አካባቢ በወንጀል መከላከል ድርጅቱን እየደገፉ ያሉ አባላት በችግኝ ተከላው መሳተፋቸውንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተፈራ በቀለ፤ ኢዜአ የተለያዩ ዘገባዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር በልማት ሥራዎች ላይ ተሳታፊ መሆኑን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ በዘገባ ሥራ በትጋት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የራሱን አሻራ በማሳረፍም ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የመገናኛ ብዙኃን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የሚሰጡትን ትኩረት የችግኝ እንክብካቤንም ተከታትለው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።