ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን የአረንጓዴ ልማት አጠናክራ ልትቀጥል ይገባል- ተመራማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን የአረንጓዴ ልማት አጠናክራ ልትቀጥል ይገባል- ተመራማሪዎች
ሐምሌ 5/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን የአረንጓዴ ልማት አጠናክራ ልትቀጥል ይገባል ሲሉ በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዎች ገለጹ።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የመሬት አጠቃቀም ፍትሃዊነትና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የሚያስችሉ የጥናት ውጤቶችን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።
በምክክሩም የጥናት ግኝቱ ውሳኔ ሰጪ የሆኑ አካላት የተገኘውን ውጤት ከነባራዊ ሁኔታው ጋር አጣጥመው እንዲሰሩ ለማድረግ እንደሚረዳ ተገልጿል።
በኢንስቲትዩቱ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተመራማሪው ዶክተር ዳዊት ውብሸት፤ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል እ.አ.አ በ1991 በብራዚሏ ሪዮ-ዴ ጄኔሮ ከተማ ባካሄዱት ውይይት ከስምምነት መድረሳቸውን አስታውሰዋል።
ከዓመታት በኋላም አገራት የሙቀት መጠን በመቀነስ የአካባቢን ደህንነት ለመጠበቅ እ.አ.አ በ2015 በፈረንሳይ ፓሪስ ባካሄዱት ምክክር ቃል መግባታቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያም በሁለቱ ታላላቅ ጉባኤዎች የተደረሱ ስምምነቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር ኢኮኖሚን እየገነባች ነው ብለዋል።
እ.አ.አ በ2010 በዴንማርኳ መዲና ኮፐንሀገን የዓለም ሙቀት መጠን መጨመርን አስመልክቶ በተካሄደው ምክክር ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል ምሳሌ ሆና መቅረቧን ተናግረዋል።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም አገራት የሚያካሂዱት የግብርና ምርት በአካባቢ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እየተገነዘቡ እንዲመጡ ማድረጉን አንስተዋል።
ኢትዮጵያም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመረችውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አጠናክራ ማስቀጠል እንዳለባት መክረዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ የደን ሃብትን በማመናመን በአካባቢና የአየር ንብረት ላይ ጫና እንደሚያሳድር አመላክተዋል።
የሕዝብ ቁጥር መጨመር ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ያለውን ጫና በመገንዘብ ለአካባቢ ምቹ የሆነ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ተመራማሪዋ ዶክተር ምንትዋብ በዛብህ፤ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ግብርና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር አጣጥሞ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ በታዳጊ አገራት ላይ ተጽዕኖው ጉልህ መሆኑን በመርህ ደረጃ ተገንዝባ እያከናወነች ያለው ተግባር ግንባር ቀደም ያደርጋታል ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ በሚል የቀረጸቻቸው ስትራቴጂዎችም በርካታ ጥቅሞችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
"ኢንስቲትዩቱ አገርን የሚጠቅሙ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ነው" ያሉት ደግሞ ሌላኛው በኢንስቲትዩቱ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ኃይለማርያም ተክለወልድ ናቸው።
የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም ፍትሃዊና ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓትን መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ለዚህም ሴቶች ከወንዶች እኩል ማስተዳደር የሚችሉትን የመሬት ባለቤትነት ሥርዓት በመፍጠር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል ሥራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።