ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ትግበራ የሶስተኛ ወገን ስምምነት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ትግበራ የሶስተኛ ወገን ስምምነት ተደረገ
ሐምሌ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ትግበራ የኢትዮጵያ መንግስት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፕሮጀክት አገልግሎት (ዩኤንኦፒኤስ) ጋር የሶስተኛ ወገን ስምምነት ዛሬ ተፈራረሟል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ እና የዩኤንኦፒኤስ ተወካይ ወርቅነሽ መኮንን ናቸው።
ፕሮጀክቱ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄደው አገራዊ የመልሶ ማቋቋም አካል ሲሆን ሁለት ዓላማዎች እንዳሉት የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል።
በስምምነቱ መሰረት ዩኤንኦፒኤስ በትግራይ ክልል ውስጥ የመልሶ መገንባት፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማሻሻልና የአየር ንብረት መቋቋም የሚችል ማህበረሰባዊ መሰረተ ልማት መገንባት ተግባራትን እንደሚያከናውን ተጠቅሷል።
ጾታን መሰረት አድርጎ በተፈጸመ ጉዳት ያጋጠማቸውን ወገኖች በተመለከተ ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ከዩኤንኦፒኤስ ጋር ስምምነት በሚፈጽም ሌላ ሶስተኛ በኩል እንደሚከናወን ተገልጿል።
ዩኤንኦፒኤስ ከመንግስት ጋር በገባው ስምምነት መሰረት ማህበራዊ ተቋማትን የሚደግፍ ሲሆን ማህበረሰቡ ጋር በመምከር ማህበረሰቡ ለሚፈልጋቸው አገልግሎቶች ፈጣን ምላሽ የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል።
በግጭት ምክንያት የተጎዱ መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚሰራ መሆኑም ተጠቁሟል።
ተቋሙ በትግራይ ክልል በስራ ላይ የሚቆየው አሁን ያለው ሁኔታ እስኪተካከልና መንግስት በክልሉ መደበኛ አገልግሎት መስጠት እስኪጀምር ድረስ እንደሆነም ተነግሯል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤