ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያላትን የብዝሃ ሕይወት ሀብት ለመጠበቅ ዘላቂነት ያለው የአካባቢ ጥበቃ ስራ ያስፈልጋል - ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ

ሐምሌ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያላትን የብዝሃ ሕይወት ሀብት ለመጠበቅ ዘላቂነት ያለው የአካባቢ ጥበቃ ስራ እንደሚያስፈልግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት በአራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዛሬ ማለዳ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ዞን በረኽ ወረዳ ቡራ ደብደቤ ቀበሌ (በድሬ ንዑስ ተፋሰስ) የችግኝ ተከላ አካሄደዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩትና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉ ተጠሪ ተቋማት ናቸው።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች በቋሚነት ባለመሰራታቸው የብዝሃ ሕይወት ሀብት ከሚደርስባቸው ጉዳት በሚፈለገው መጠን አላገገሙም።

የአፈር መሸርሸር፣ የመሬት መራቆትና ሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለብዝሃ ሕይወቱ ፈተና መሆናቸውን ገልጸዋል።

“ውሃ የራሱ ሕይወት እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ የውሃ ሀብትን ለመጠበቅ ወጥነት ያለው የተፋሰስ ልማት ስራ ማከናወን እንደሚገባ አመልክተዋል።

ውሃ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በውል በመገንዘብ ሁሉም ሕብረተሰብ የውሃ ዳርቻ እንክብካቤ ስራ ማከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል።

ዘላቂነት ያለው የአካባቢ ጥበቃ ስራ በማከናውን አካባቢን፣ ግድቦችን፣ ስነ-ምህዳርና የተፈጥሮ ሀብቶችን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አንዱ ግብ ኢትዮጵያ ያላትን ብዝሃ ሕይወት ከአደጋ መጠበቅና መንከባከብ እንደሆነ ገልጸው፤ ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ተግባር በዘላቂነት መከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ማህበረሰቡ የችግኝ ተከላውን “ምግቤን ከጓሮዬ” በሚል ከተጀመረው እንቅስቃሴና ሌሎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚከናወኑ ስራዎች ጋር አስተሳስሮ መተግበር እንዳለበት ጠቁመዋል።

የችግኝ ተከላ የተካሄበት የድሬ ንዑስ ተፋሰስ አካባቢ ያለውን የብዝሃ ሕይወት ሀብት ከጉዳት ለመጠበቅ ለሚከናወኑ ስራዎች ሚኒስቴሩ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ለቀጣዩ ትውልድ የተራቆተ መሬት ሳይሆን የበረከት ምድር ለማስረከብ እንዲቻል የአካባቢ ጥበቃ ስራ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግም አክለዋል።

የበረኽ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ አሽኔ ዳዲ በበኩላቸው ወረዳው ባለው ብዝሃ ሀብት ሕይወትና በምርታማነቱ ይታወቅ እንደነበር አስታውሰው፤ የአፈር መሸርሸር፣ የመሬት መራቆትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምርታማነቱ እንዲቀነስና የተፈጥሮ ሀብቱ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጉን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካባቢው ብዝሃ ሕይወቱ ከደረሰበት ጉዳት እንዲያገግም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም