የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አማራጭ የግብር ክፍያ ስርአት ተግባራዊ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አማራጭ የግብር ክፍያ ስርአት ተግባራዊ አደረገ
ሐምሌ 5/2014 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በተያዘው በጀት ዓመት አማራጭ የግብር ክፍያ ስርአት ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ፤ የበጀት አመቱ የግብር መክፈያ ጊዜ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በይፋ መጀመሩን ተናግረዋል ።
የግብር ማሳወቂያ ጊዜ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 01 እስከ ሐምሌ 30/2014፣ የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 01 እስከ ጳጉሜ 05/2014 ዓ.ም እንዲሁም የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 01/2014 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30/2015 ዓ.ም መሆኑን ገልፀዋል።
በ2015 በጀት አመት 70 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸው ከሐምሌ 01ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30ቀን 2015 ዓ.ም የዕቅዱን 42 በመቶ ለማሳካት ታቅዷል ብለዋል።
በቢሮው የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን እና የተለያዩ አማራጭ የግብር መክፈያ አሰራር ተግባራዊ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት በማድረግ ግብር ከፋዮች በቴሌ ብር በኩል ክፍያ እንዲፈፅሙ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ ታክስ መክፈል የሚችሉበት አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።
በዚህ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በተቀመጠላቸው የግብር መክፍያ ጊዜ ተገኝተው በቀረቡላቸው የክፍያ አማራጮች እንዲከፍሉም ጥሪ አቅርበዋል ።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ግብር ሲከፍሉ ያገኘናቸው አቶ ፈቃዴ አሰፋ እና አቶ ሰለሞን ይርጉ፤ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መክፈል ለሁሉም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በግብር ክፍያ ወቅት ከኔትወርክ እና ሲስተም ጋር የሚስተዋሉ ችግሮች በዘላቂነት መፈታት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።