ሀገራዊ አንድነትና ፍቅር እንዲጠናከር የሚደግፉ መሆናቸውን የአርባምንጭ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ አንድነትና ፍቅር እንዲጠናከር የሚደግፉ መሆናቸውን የአርባምንጭ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ
አርባምንጭ መስከረም 3/2011 ሰላምን በመጠበቅ ሀገራዊ አንድነትና ፍቅር እንዲጠናከር በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ በአርባምንጭ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ፡፡ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማዋ ወጣቶች እንዳሉት የመጪው ጊዜ ብሩህ ተስፋ እንዲለመልም አንድነት ያስፈልጋል፡፡ በሼቻ ክፍለ ከተማ የቤሬ ቀበሌ ወጣት ከበደ ካሣ በሰጠው አስተያየት ወጣቱ ለለውጥ ያደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ ስፍራዎች የርስ በርስ ግጭቶች ቢከሰቱም እየታየ ያለው ዴሞክራሲ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዴሞክራሲም ሆነ በልማቱ የወጣቱ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ መያዝና አንድነቱን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁሟል ፡፡ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ በዋዜማው ታስበው ያለፉት የሰላም ፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የመደመርና የአንድነት ቀናት ቀጣይነት ኖሯቸው እንዲጠናከሩ የሚደግፍ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዓባያ ክፍለ ከተማ የወዜ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ዋሴ ዋና በበኩሉ ከዚህ ቀደም የነበረው ብሔር ተኮር ፖለቲካ በወጣቱ አስተሳሰብ ላይ አሉታዊ ጫና በመፍጠሩ ወቅቱ የሚጠይቀውን ሀገራዊ ፍቅር እንዳይኖር ማድረጉን ጠቅሷል፡፡ የአንድነት ቀን ሲታሰብ እኔ ከሚል ስሜት በመውጣት የእኛነት አስተሳሰብ የያዘበት ዕለት መሆኑን ገልጿል ፡፡ " የሀገራችን ሰላምና ለውጥ ዋስትና ሊኖረው የሚችለው በአንድነት ብቻ በመሆኑ አንድነታችን እንድናጠናክር የበኩሌን እወጣለሁ" ብሏል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ ተከባብረው በአንድነት የመኖር ታሪክ ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ በነጭ ሳር ክፍለ ከተማ የውሃ ምንጭ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ከዲር መሃመድ ነው፡፡ የህግ የበላይነት እንዲከበርና በአካባቢው ለሚከወነው ነገር ሁሉ ኃላፊነት በተሞላ መልክ ለመንቀሳቀስ ወጣቱም ተደምሮ ለውጥ እንዲያመጣ የበኩሉን እንደሚወጣ ጠቁሟል ፡፡ ሌላው የከተማዋ ወጣት ብዙነህ ዘርፉ " ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ከፍታ ዘመን በሚል መርህ ቃል አክብረናል ፤ዘንድሮ ደግሞ በፍቅር ተደምረን በይቅርታ እንሻገር የሚለው መርህ እኛ ወጣቶች በተግባር ማሳየት ይገባናል " ብሏል፡፡ በቤተሰብ ደረጃም ቢሆን አንድነት ከሌለ የሚፈርስ እንደመሆኑ ለውጡን በመጠቀም ሀገራዊ አንድነት እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡