የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ
ሐምሌ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት በአራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዛሬ ማለዳ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ዞን በረኽ ወረዳ ቡራ ደብደቤ ቀበሌ (በድሬ ንዑስ ተፋሰስ) የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የውሃና ኢኒርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች፣ የተቋማቱ ሰራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩትና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉ ተጠሪ ተቋማት ናቸው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአራት ዓመት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን እስካሁን ባለፉት ሶስት ዓመታት 18 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞች እንደተተከሉ መገለጹ ይታወሳል።
በዘንድሮው መርሃ ግብር ከስድስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ታቅዶ በአገር አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤