ቀጥታ፡

የምክር ቤት አባላት በተወከሉባቸው አካባቢዎች በአካል በመገኘት የህዝቡን አይነተኛ ችግሮች ለመፍታት መስራት አለባቸው

ሐምሌ 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት በተወከሉባቸው አካባቢዎች በአካል መገኘት የህዝቡን አይነተኛ ችግሮች ለመፍታት እንዲሰሩ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጠየቁ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላትና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ 'ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨርቲ አሊቬሽን' ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ያገኙትን የትምህርት ቁሳቁስ በተመረጡበት ወረዳ 12 ለሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ለግሰዋል።

የምክር ቤት አባሏ ድጋፍ ያደረጉት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፊሊጶስ ትምህር ቤት ሲሆን ከ400 በላይ የአጸደ ህጻናት ተማሪዎች የሚውል ከአንድ ሚሊየን 300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ነው።ድጋፉንም የቻይና ኤምባሲ፣ የድርጅቱ ተወካዮች እና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኅላፊዎች በተገኙበት ለትምህርት ቤቱ አስረክበዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የወረዳው ነዋሪዎች የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት በተወከሉባቸው አካባቢዎች በአካል በመገኘት የህዝቡን አይነተኛ ችግሮች ለመፍታት መስራት አለባቸው ብለዋል።

ወረዳውን ወክለው የተመረጡት ወይዘሮ ሌሊሴ ያደረጉትን መልካም ተግባር ለሌሎች የምክር ቤት አባላትም እንዲከተሉት ጠይቀዋል።

የምክር ቤት አባላት አጋር አካላትን በማስተባበር ከሰሩ የተቸገሩ ወገኖችን ከማገዝ ባለፈ የማህበረሰቡን ችግሮች መፍታት የሚችሉ መሆኑን ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባላት በተለይም በእረፍት ጊዜያቸው በወከላቸው ህዝብ መካከል በመገኘት የህዝብ አደራቸውን ቢወጡ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የወከሉትን ህዝብ ማወያየት፣ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ማስተባበርና አቅመ ደካሞችን የመደገፍ ስራ ላይ በስፋት እንዲሳተፉም ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኅላፊ ዘላለም ሙላቱ የትምህርት መስክ የትውልድ ግንባታ በመሆኑ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ትብብር ይጠይቃል ብለዋል።

ቻይና ፋውንዴሽን ፎር ፖቨርቲ አሊቬሽን' ቀደም ብሎ በሁለት ትምህርት ቤቶች ምገባ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀው፤ በዕለቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

በተለይም የምክር ቤት አባላት እንዲህ አይነት በጎ ተግባራትን በማስተባበር የድርሻቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በተመረጡበት አካባቢ በመገኘት ያደረጉት ድጋፍ የመጀመሪያቸው መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፤ በቀጣይ የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በክረምቱ ከአረንጓዴ አሻራ በተጨማሪ የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስና ማዕድ ማጋራት ተግባራት ላይ የሚሳተፉ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም