ኢትዮጵያን ለማሻገር ከችግሮች ይልቅ መልካም ነገሮች ላይ ማተኮር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ለማሻገር ከችግሮች ይልቅ መልካም ነገሮች ላይ ማተኮር ይገባል
አርባ ምንጭ፤ሐምሌ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ፈተና እንድትሻገር ከችግሮች ይልቅ መልካም ነገሮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሚዛን አማንና የአርባ ምንጭ ከተሞች ነዋሪዎች ተናገሩ።
የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ጠላቶች የተለያዩ ክፍተቶች እየፈለጉ በሀገርና በህዝብ ላይ ፈተናዎችን ለማብዛት ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሚገኙ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
ፈተናውን ለመሻገር ጠላት የሚፈጥረውን ችግርና አጀንዳ ከማራገብ ይልቅ መልካም ነገሮችን በማጉላት ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸው፤ አሉባልታዎችን ከሚያስፋፉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በመራቅ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ መተባበር አለብን ብለዋል።
አሸባሪዎች በየአካባቢው ግጭት በመፍጠር የዜጎችን ፈተና እያበዙ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታት ላይ ብቻ እንዲጠመድ የሚያደርጉ እኩይ ሥራዎችን ለመመከት ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።
መንግስት የልማት ሥራዎች ሳይቆሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረትም አድንቀው፤ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ክብር አስጠብቆ ማስቀጠል የሚቻለው ጠንክሮ በመስራት እንጂ በማህበራዊ ሚዲያ አሉባልታ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው እንደ ሀገር ተስፋ ሰጪ ልማቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተው፤ የልማት ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግና ሀገርን ለማስቀጠል በአንድነት መቆምና መተባበር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
አሸባሪዎች ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ መጨፍጨፋቸው የሚወገዝና መሸነፋቸውንና ተስፋ መቁረጣቸውንማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቱን የብሔር መልክ በማስያዝ ዜጎችን እርስ በርስ ለማጋጨትና ሀገር የማፍረስ እኩይ አላማቸውን ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል።
ተስፋ ሰጭ የልማት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አመልክተው፤ የፀጥታ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል ላይ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተስፋ መሆኑን ተናግረው፤ የኢትዮጵያ የእድገት ግስጋሴን በአሸባሪዎች እንደማይደናቀፍ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።