ምክር ቤቱ በጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ በጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታወቀ
ሐምሌ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዴሞክራሲን ስርዓትን በሕግ ስርዓት ውስጥ ለመገንባት በጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚደረግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ ያዘጋጀው የዴሞክራሲ ተቋማት በሆኑት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተርና የመገናኛ ብዙኃን የማሻሻያ የለውጥ ስራዎችን የተመለከተ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ ያከናወኗቸውን የለውጥ ስራዎች ያቀረቡት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሠው ኃይልና በአደረጃጀት ረገድ የተለያዩ ስራዎች መስራታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የሕግ ማዕቀፎችን በማሻሻል፣ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋትና ባለሙያዎችን በሙያ በማደራጀት የለውጥ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም ተቋማቱ ቀደም ሲል ከነበረው የላቀ ስኬት እንዳስመዘገቡ ጠቅሰው፤ የአስፈጻሚ አካላት ገለልተኛ አለመሆንና የቁጥጥር ማነስ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አንስተዋል።
የዴሞክራሲ ተቋማቱን እንቅስቃሴ ለማሳደግ በተከናወኑ ስራዎችን ላይ ማብራርያ የሠጡት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ ገለልተኛ የሆነ ዘላቂ የዴሞክራሲ ተቋም የመገንባት ጉዳይ አንገብጋቢ ነው ብለዋል።
ተቋማቱን በአሠራር፣ በሠው ኃይልና በቴክኖሎጂ መገንባት በትኩረት መሰራት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱ በተቋማቱ የቀረቡለትን ሪፖርቶችና ተቋማት ያሳለፉትን ህጋዊ ውሳኔ የማስፈፀም፣ የማጣራትና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
ግንዛቤ ማስጨበጥና ማስተማር ትኩረት እንደሚሰጠው አመልክተው፤ ይህም የተቋማቱን እንቅስቃሴ ከማሳወቅ ባለፈ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ያስችላል ብለዋል።
በተለይም መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ለህብረተሱ እንዲደርስ በትጋት መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፤ ምክር ቤቱም ክትትሉን ያጠናክራል ነው ያሉት።
በተጀመረው የ2015 በጀት ዓመት በጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚደረግ ያመለከቱት አፈ-ጉባኤው፤ ይህም የዴሞክራሲ ስርዓትን በሕግ ስርዓት ውስጥ ለመገንባት ያስችላል ብለዋል።
የዴሞክራሲ ተቋማት አደረጃጀትና የማሻሻያ ጉዳዮች ህግን ጠብቀው የሚሰሩበት መንገድ መጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር፣ የመገናኛ ብዙኃንና የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤