ቀጥታ፡

በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደው እርምጃ የምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ ነው-በዞኑ የልዩ ሃይል ዋና አዛዥ

ሐምሌ 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደው ጠንካራ እርምጃ የምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የምዕራብ ወለጋ ዞን ልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ኮማንደር ነገራ ዱፌራ ገለጹ።

በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ዋና አዛዡ አረጋግጠዋል።

አሸባሪው በደረሰበት ከባድ ምት በሽሽት ላይ እያለ በቶሌ ቀበሌ በንጹኃን ዜጎች ላይ ጭካኔ የታከለበት ጭፍጨፋ መፈጸሙን አስታውሰው በተወሰደበት እርምጃ ዘርፎ የወሰዳቸው ንብረቶች እየተመለሱ መሆኑን ገልጸዋል።

የጸጥታ ሃይሉ የአካባቢው መልክአ ምድር ሆነ የአየር ንብረት ተጽዕኖ ሳይበግረው የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑንም ኮማንደር ነገራ ዱፌራ ጠቅሰዋል።

በመከላከያ ሰራዊትና በክልሉ የጸጥታ ኃይል የተቀናጀ እርምጃ የምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ዋና አዛዡ እንደሚሉት የሽብር ቡድኑን በማጥፋት በህዝብ ላይ ድጋሚ ጥቃት እንዳያደርስ ለማድረግ የጸጥታ ሃይሉ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።

የጸጥታ ሃይሉ የህዝብን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የሽብር ቡድኑ ይንቀሳቀስባቸው በነበሩ አካባቢዎች ሁሉ የተቀናጀ የኦፕሬሽን ስራ ላይ ይገኛል ብለዋል።

እየተካሄደ በሚገኘው ህግና ስርዓትን የማስከበር ተግባር አሸባሪው ሸኔ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንዳጋጠመው ጠቁመዋል።

በአሸባሪ ቡድኑ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ኮማንደር ነገራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም