የጀርመኑ ''ስሪ ፖይንት'' ከመስከረም 2015 ዓ.ም አንስቶ በኢትዮጵያ የታዳጊዎች እግር ኳስ ስልጠና መስጠት ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የጀርመኑ ''ስሪ ፖይንት'' ከመስከረም 2015 ዓ.ም አንስቶ በኢትዮጵያ የታዳጊዎች እግር ኳስ ስልጠና መስጠት ይጀምራል
ሀምሌ 3/2014/ኢዜአ/ የጀርመኑ ስሪ ፖይንት ከመስከረም 2015 ዓ.ም አንስቶ በኢትዮጵያ የታዳጊዎች እግር ኳስ ስልጠና መስጠት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታወቀ።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንዳሉት የስልጠና ማዕከላት ከፍቶ ታዳጊ ወጣቶችን ማሰልጠን የክለቦችና የግለሰቦች ሃላፊነት ቢሆንም አሁን ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ በተቃራኒ ነው።
ለዚህ ደግሞ የሀገሪቱ የእግር ኳስ ክለቦች አደረጃጀትና የስራ ፍቃድ አሰጣጥ ያልተስተካከለ መሆኑ ክለቦች በሚጠበቅባቸው ልክ እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል።
በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት በሚችለው አቅም ታዳጊዎችን በስፋት ለማብቃት የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም ፌዴሬሽኑ በጥር 2014 ዓ.ም ስሪ ፖይንት ከተባለና በህጻናት እግር ኳስ ስልጠና ላይ ከሚሰራ የጀርመን ድርጅት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የታዳጊዎች እግር ኳስ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት መፈጸሙን ተናግረዋል።
በዚህም ድርጅቱ ከመስከረም 2015 ዓ.ም አንስቶ ስልጠና መስጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል።
ለስልጠና የሚገቡ ታዳጊዎች ምልመላ በቅርቡ በሚካሄደው የክልሎችና ክለቦች ከ17 ዓመት በታች ውድድር እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
ለስልጠናው ብቁ ሆነው የሚመለመሉት ታዳጊዎች በየጊዜው እየተመዘኑ በሚያስመዘግቡት ውጤት መሰረት የመተካት ሂደት እንደሚኖር ነው የተናገሩት።
ስልጠናው በጊዚያዊነት በአዲስ አበባ አያት አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልህቀት አካዳሚ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ስሪ ፖይንት በስልጠናው ታዳጊዎችን በማብቃት ለአውሮፓና በሌሎች ሀገራት ለሚገኙ ክለቦች በማዘዋወር ከሚገኘው ገንዘብ 60 በመቶውን የሚወስድ ሲሆን ቀሪውን 40 በመቶ ፌዴሬሽኑ የሚያገኝ ይሆናል።
የፌዴሬሽኑ ግብ በዋናነት ከሚገኘው ገንዘብ ይልቅ ታዳጊዎቹ በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች እድል አግኝተው ራሳቸውና ቤተሰባቸውን አለፍ ሲልም ሀገራቸውን የሚጠቀሙበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።
የስልጠናው ስኬታማነት ሌሎች ታዳጊዎች ህልማቸውን እውን ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት ለመጨመር በጎ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።
ይህ ስልጠና መጀመር ለብሄራዊ ቡድን መጠናከር የራሱ በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የገለጹት።