ወጣቶች የኢትዮጵያ አንድነት፣ አብሮነት እና መተባበር እንዲጠናከር ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው-የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች የኢትዮጵያ አንድነት፣ አብሮነት እና መተባበር እንዲጠናከር ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው-የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም
ሀምሌ 3/2014/ኢዜአ/ “አገር ተረካቢ ወጣቶች የኢትዮጵያ አንድነት፣ አብሮነት እና መተባበር እንዲጠናከር ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው” ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።
የአራተኛው ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ስልጠና በጅማ ዩኒቨርስቲ ተጀምሯል።
በዚህ ወቅት የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም የስልጠናው ዓላማ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአገር ግንባታ ስራ ማሳለጥና ከግብ እንዲደርስ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣቶች አብሮ ለመስራት ፣ ያላቸውን ዕውቀት እና ልምድ ለመለዋወጥ እንዲሁም ሕዝባቸውን በቅንነት ለማገልገል ይረዳል ብለዋል።
የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶች የኢትዮጵያ አንድነት፣አብሮነት እና መተባበር እንዲጠናከር የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በአራተኛው ዙር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ሶስት ሺህ ወጣቶች ለአንድ ወራት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ይወስዳሉ።
በተመሳሳይ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ስልጠና ዛሬ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መስጠት ተጀምሯል።
በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የመርሃ ግብሩ መዳረሻ ግብ ወጣቶች ማህበራዊ እሴቶችና የሞራል አቅም እንዲጎለብት በመደገፍ በኢትዮጵያ እርስ በእርስ መደማመጥና መረዳዳትን ማምጣት ነው።
ከጭፍን ጥላቻ ወጥቶ እርስ በእርስ የተጋመደ ማህበረሰብ እንዲፈጠር በማድረግ ዘላቂ ሰላምና አገራዊ መግባባትን ማስፈን እንዲሁም ኢትዮጵያዊ እሴቶችንና መርሆዎችን ለወጣቱ ትውልድ የማስተላለፍ ራዕይ መሰነቁን ገልጸዋል።
ዛሬ በጅማ፣ በሐዋሳና ዋቸሞ ዩኒቨርስቲዎች ከስምንት ሺህ በላይ ወጣቶች የብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ስልጠና ተጀምሯል።
ከዚህ ቀደም በነበሩ የሶስት ዙር ስልጠናዎች ከዩኒቨርስቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ የተመረቁ 23 ሺህ ወጣቶችን በማሰልጠን ወደ ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉን ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።