ኤርትራ ሆኖ ሲታገል የነበረው የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ዛሬ አዲስ አበባ ገባ

አዲስ አበባ መስከረም 3/2011 መቀመጫውን ኤርትራ በማድረግ በትጥቅ ትግል ላይ የነበረው የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ገባ። በንቅናቄው ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ኡማን ጎራ የሚመራው ልፁክ ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ሲገባ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ እና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኦሌሮ ኦፒው አቀባበል ተደርጎለታል። የንቅናቄው ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ ኡማን ጎራ ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው አገር ወስጥ የተጀመረውን ለውጥ በማየትና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የሰላም ጥሪ በመቀበል ነው ብለዋል። ከጋምቤላ ህዝቦች ጋር በመሆን የተጀመረውን የለውጥና የመደመር ስራ ለማገዝ እንሰራለን ብለዋል። ወደ ትጥቅ ትግል ያስገባን የአገሪቱ ህገ-መንግስት እና የሰብዓዊ መብቶች በአግባቡ ባለመተግበሩ ነው ያሉት ምክትል ሊቀ-መንበሩ አሁን በሰላም በመወያየት ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ከህዝብና ከመንግስት ጋር በመሆን እንታገላለን ብለዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በበኩላቸው ውጭ ሆነው በትጥቅ ሲታገሉ የነበሩ ድርጅቶች በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መምጣታቸው የመንግስት ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል። አሁን ላይ የጦርነትና የአመፅ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ቀስ በቀስ በማስወጣት የውይይት ፖለቲካን ለማራመድ አጋዥ እንደሆነ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ኦሌሮ ኦፒው በበኩላቸው ንቅናቄው የሰላም ጥሪ አካል ሆነው በመምጣታቸው የክልሉን ህዝብ ጥቅምና ሰላም ለማስጠበቅ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ብለዋል። ከክልሉ መንግስትና ከህዝቡ ጋር ሆነው ለክልሉ ብልፅግና እንዲሰሩ አሳስበው ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል። የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቀናቄ በ1976 ዓ.ም መመስረቱንና ደርግን ለመጣል ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን መታገሉን የንቅናቄው ምክትል ሊቀ-መንበር ተናግረዋል። በኤርትራ መታገል ከጀመረ 10 ዓመት ማስቆጠሩንም እንዲሁ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም