ቀጥታ፡

የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግር እየተፈታ ነው

ባህርዳር መስከረም 3/2011 መንግስት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግርን  ለመፍታት እየወሰደ ያለው የማስተካከያ እርምጃ አበረታች ውጤት እያገኘ መሆኑን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባህር ዳር ዲስትሪክት አስታወቀ። በሁለት ወር ውስጥ አስር ሚሊዮን 400ሺህ ዶላር በግዥና በዝውውር ተሰብስቧል። በዲስትሪክቱ አለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ሃይሌ ሙሃመድ ለኢዜአ እንደገለፁት በጥቁር ገበያ መስፋፋትና በሌሎች ምክንያቶች ተፈጥሮ የነበረው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት ችግር እየተፈታ ነው ። በሐምሌና ነሐሴ 2010 ዓ.ም. ብቻ በዝውውር ስምንት ሚሊዮን 500ሺህ  ዶላርና በግዥ ደግሞ አንድ ሚሊዮን 900ሺህ ዶላር ተሰብስቧል። "ተፈጥሮ በነበረው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት በኢንቨስትመንትና በውጭ ንግድ በተሰማሩ ባለሃብቶች ይቀርብ ለነበረው የዶላር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከስድስት ወር በላይ ይፈጅ ነበር " ብለዋል ። መንግስት የማስተካከያ እርምጃውን መውሰዱ የዶላር አቅርቦቱ መሻሻል መጀመሩን ተናግረዋል ። አሁን ላይ በቂ የዶላር መጠባበቂያ ክምችት በመኖሩ ለባለሃብቶችም ሆነ ነጋዴዎች የዶላር ጥያቄ ባቀረቡ ከ15 እስከ 30 ቀናት ውስጥ ምላሽ እየተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰዋል ። "የዶላር ምንዛሬው በዲስትሪክቱ ስር ባሉ 81 ቅርንጫፍ ባንኮች እየተካሄደ ነው" ያሉት ስራ አስኪያጁ መንግስት ያደረገውን ጥሪ ተቀብለው ዶላር ለመመንዘር ወደ ባንኮች ለሚመጡ ደንበኞች የቅድሚያ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል። የዶላር ክምችት ያላቸው ግለሰቦች ያለስጋት ወደ ባንኮች በመመጣት እንዲመነዝሩ ጥሪ አቅርበዋል ። ወጣት ሰላማዊት ገብሩ ለ13 ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ከውጭ የሚላክላትን ዶላር ስትመነዝር መቆየቷን ተናግራለች ። "ከዘመዶቼ ይላክልኝ የነበረው ዶላር በጥቁር ገበያ ተመንዝሮ ይደርሰኝ ነበር" ያለው ደግሞ ወጣት ተመስገን ተስፋ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዶላሩ በህጋዊ መንገድ በባንኮች እየተላከለት መሆኑን ተናግሯል ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባህር ዳር ዲስትሪክት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በግዥና በዝውውር ከ29 ሚሊዮን 900ሺህ  ዶላር በላይ ክምችት መሰበሰቡ ታውቋል ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም