በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የአመራር ክፍተቶችን ለማሻሻል የተቋማትን ራዕይ ሊያሳካ የሚችል የስትራቴጂክ መሪነት ስልትን ማዳበር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የአመራር ክፍተቶችን ለማሻሻል የተቋማትን ራዕይ ሊያሳካ የሚችል የስትራቴጂክ መሪነት ስልትን ማዳበር ይገባል

ሐምሌ 2/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የአመራር ክፍተቶችን ለማሻሻል የተቋማትን ራዕይ ሊያሳካ የሚችል የስትራቴጂክ መሪነት ስልትን ማዳበር እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
ትኩረቱን በአመራር ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ያደረገው "የአመራር ክህሎት" የተሰኘ መጽሃፍ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል።
መጽሃፉ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትና የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ ተስፋየ ነዋይ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ312 ገጾች ለአንባብንያን ቀርቧል፡፡
መጽሃፉ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ ድንቅ ስራ ሰርተው ያለፉ መሪዎችን የአመራር ጥበብ አካቷል።
አቶ ተስፋየ ነዋይ መጽሃፉን በሚመለከት ባቀረቡት ገላጻ፤ በመጽሃፉ በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ መሪ ሊኖረው የሚገቡ የክህሎት፣ ብቃት፣ ችሎታና ሌሎች የአመራርነት ጥበቦችን መያዙን አስረድተዋል።
ከአመራር ጋር በተያያዘ በተጨባጭ ያሉ ችግሮችንም በማካተት ለውጤታማ መሪነት የሚያግዙ ስልቶችንና ክህሎቶችን ደራሲው በመፍትሄነት አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ ለውጥ የመምራት ክፍተት፣ ውሳኔዎች ተፈጻሚ አለመሆን፣ በስብሰባ የሚጠፋ ጊዜና ሌሎች ችግሮችን በሚመለከትም ግልጽ ማብራሪያ መያዙን ጠቁመዋል፡፡
የጊዜ አጠቃቀምን ጨምሮ ከተጠቀሱት ችግሮች ለመውጣት የሚያግዙ መፍትሄዎችንም ያመላክታል ነው ያሉት፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ማዓዛ አሸናፊ በበኩላቸው ስትራቴጂክ መሪነትን ለማዳበር ዘወትር ግብን መሰረት ያደረገ ስራ መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አበረ አዳሙ፤ ደራሲው በኃላፊነት ላይ በመሆን ህዝብን ከማገልገል በተጓዳኝ በአመራር ክህሎት ላይ ያተኮረ መጽሃፍን ለአንባብያን ማብቃታቸው የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ደራሲው ቀደም ሲል የፕሮጀክት አመራር ሳይንስና ጥበብ፣ህግና አተረጓጎሙ የተሰኙ መጽሃፍትን ጨምሮ 3 መጽሃፎችን ለአንባብያን አብቅተዋል።
"የአመራር ክህሎት" የተሰኘ መጽሃፍ በዓለምና በኢትዮጵያ ስኬታማ የአመራር ጥበብ የነበራቸው መሪዎችን የያዘና በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ የመሪነት ክፍተቶችን የዳሰሰ መሆኑን መጽሃፉን የተቹት ሙያተኞች ገልጸዋል።