አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ባህላዊና በተፈጥሮ ይዘታቸው የበለፀጉ ምግቦችን ለዓለም የሚያስተዋውቅ መፅሐፍ አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ባህላዊና በተፈጥሮ ይዘታቸው የበለፀጉ ምግቦችን ለዓለም የሚያስተዋውቅ መፅሐፍ አስመረቀ
ሐምሌ 2 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ባህላዊና በተፈጥሮ ይዘታቸው የበለፀጉ ምግቦችን ለዓለም ሀገራት ለማስተዋወቅ የሚረዳ በበረራ የምግብ አዘጋጆች የተሰናዳ ”Fly Ethiopian Go Organic Recipe Book” የተሰኘ መፅሐፍ ዛሬ አስመርቋል።
መፅሐፉ በውስጡ ያካተታቸው ይዘቶችና ዓላማው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አየር መንገዱ የበረራ ደንበኞቹን ፍላጎት ያሟላ የምግብ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡
በዚህም ለመንገደኞች የተለያዩ ጣፋጭ የሆኑ እና ሀገራዊ ባህልን የሚያንጸባርቁ የምግብ ዓይነቶችን እያቀረበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የአየር መንገዱ የበረራ ምግብ ዝግጅት ባለሙያዎች የሀገሪቱን ባህላዊ እና በተፈጥሮ ይዘታቸው የበለፀጉ ምግቦችን ለዓለም ሀገራት ለማስተዋወቅ ፕሮጀክት ነድፈው እንቅሰቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን የሁሉም አካባቢ ባህላዊ ምግቦችንና በተፈጥሮ የበለጸጉ ምግቦችን ዝርዝር የያዘ ”Fly Ethiopian Go Organic Recipe Book” የተሰኘ መፅሐፍ ማዘጋጀታቸውን ነው ያነሱት።
መፅሐፉም በውስጡ የኢትዮጵያን የተለያዩ አካባቢዎች የምግብ አሰራሮችን እና ዓይነታቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
መንገደኞች በጉዞ ወቅት የሚቀርቡላቸው የምግብ ዓይነቶች ተፈጥሮአዊ ይዘታቸውን የጠበቁ መሆናቸውንና ከጤናና ተያያዥ ሁኔታ አንጻር ፍላጎታቸውን ያሟሉ ስለመሆናቸው እንዲያውቁ ይረዳል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣይም የኢትዮጵያን የስነ ምግብ ባህል፣ እውቀት እና ጥበብ ለዓለም ሀገራት ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው ምግብ የአንድ ሀገር መገለጫ ከመሆኑ ባሻገር ራሱን የቻለ የቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፤በምግብ ቱሪዝም ላይም በርካታ ሀገራት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም ጃፓን ባህላዊ ምግቦቿን በማስተዋወቅ በኢትዮጵያ የምግብ ቱሪዝም እንቅሰቃሴ ማድረጓን በአብነት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያዘጋጀው መፅሐፍም ኢትዮጵያን ለተቀረው ዓለም በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
አየር መንገዱ በሚሄድበት ሁሉ በመጽሐፉ የተካተቱ የኢትዮጵያ ምግቦችን የሚቀምሱ መንገደኞች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያነሳሳልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰብ ሀገር እንደመሆኗ ብዙ ዓይነት ባህላዊና በተፈጥሮ የበለጸጉ ምግብ ዓይነቶች ባለቤት ናት ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህንን ፀጋ ለዓለም በማስተዋወቅ የቱሪዝም ዘርፉን ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያን ምግቦች ዝርዝር ለደንበኞቹ በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን የምግብ ቱሪዝም አስጀምሯል፤ በዚህም ኩራት ይሰማናል ነው ያሉት።
የቱሪዝም ሚኒስቴር በቀጣይ የምግብ ቱሪዝምና ተያያዥ ጉዳዮችን በማጠናከር የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ