ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት አርቆ የሚያስብ ትውልድ መፍጠር ላይ ተግቶ መስራት ይገባል- ፕሮፌሰር ጄይላን ወሊዬ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት አርቆ የሚያስብ ትውልድ መፍጠር ላይ ተግቶ መስራት ይገባል- ፕሮፌሰር ጄይላን ወሊዬ
ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 2/2014(ኢዜአ) ፡- አርቆ የሚያስብ ትውልድ መፍጠር ላይ በመረባረብ የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ተግቶ መስራት እንደሚገባ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጄይላን ወሊዬ ተናገሩ።
ሰላማዊ የመማር ማስተማር ተግባራትን ማጠናከር በሚያስችሉና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የሁለት ቀናት ውይይት በድሬዳዋ ተካሂዷል፡፡
ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን በተቀናጀ መንገድ ለማጠናከር የሚያግዝ ሁሉን አካታች የተማሪዎች ህብረት ኔት ወርክም ተመስርቷል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሣተፉት ፕሮፌሰር ጄይላን ወሊዬ እንዳሉት፤ ለሀገር ቀጣይ ከፍታ መረጋገጥ በሞራል የተገነባና ነገን አሻግሮ የሚመለከት ትውልድ ማፍራት ላይ መረባረብ ይገባል፡፡
በምክንያታዊነት የሚያምን ዜጋ በመፍጠር የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ ላይ መትጋትም እንዲሁ።
የተማሪዎች ህብረትን ማሳደግ፣ አደረጃጀታቸውን ማጠናከርና ማሻሻል የነገ አርቆ አሳቢ መሪዎችን በእርግጠኝነት ለመፍጠር ያስችላል፤ የአለምና የሀገራችን ታላላቅ መሪዎች ከዚህ የመነጩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የኔትወርኩ መመስረት በአሁናዊ ጭጋጎች ውስጥ መጠላለፍና መውደቅ ሣይሆን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የግጭት መንገዶችን በመለወጥ በተቀናጀና ሁሉን አካታች የሰላም መንገድን ለመከተል አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ፕሮፌሰር ጄይላን ተናግረዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አወቀ አጥናፉ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ እና ከፍታ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች የሚረከቧትን ሀገር ቀጣይ ዕጣ ፋንታ የሰመረ ለማድረግ በምስራቁ ዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረው ሁሉን አካታች የተማሪዎች ህብረት ኔትወርክ አበርክቶው የጎላ ይሆናል ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዘዳንት ተማሪ ናትናኤል ዳንኤል ፤ በዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማሩ ሥራ ውጤታማ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ በአግባቡ ወደ ተግባር ለመለወጥና ያለፉ ስህተቶችን ማረም የሚቻልባቸውን መንገዶች የተካሄደው ውይይት ወሳኝ እንደነበር ገልጿል፡፡
ውይይቱ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሊፈጠር የሚችልን ግጭት በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል ያግዛል ያለችው ደግሞ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች የሰላም ፎረም አስተባባሪ ተማሪ ረሀማ ያሲን ናት።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በተካሄደው ውይይት ማጠናቀቂያ በሀረማያ፣ በድሬዳዋና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ህብረት መካከል የተቀናጀ ሥራ ማከናወን የሚያስችል ሁሉን አካታች ኔትወርክ የተመሠረተ ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች፣ የትምህርት እና የሠላም ሚኒስትርና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል፡፡