ቀጥታ፡

ለሆስፒታሉ ከ1 ቢሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ

ሐረር፤ ሐምሌ 2/2014 (ኢዜአ) የፌዴራል ሐረር ፖሊስ ሆስፒታል ከ1 ቢሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ ዛሬ የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደበላሽ ገብረሚካኤል እና የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ናቸው።

ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በወቅቱ  የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ግንባታ በምስራቅ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ለሰራዊቱ አባላት እና ቤተሰቦች እየሰጠ የሚገኘውን የህክምና አገልግሎት ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያደርሰው ገልጸዋል።

ለአጎራባች ሀገራት ጭምር  አገልግሎት በመስጠት የህክምና ቱሪዝምን የማሳደግ ስራን እንደሚያጎለብተው ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ  ዜጎች   ለተሻለ ህክምና ወደሌላ ሀገር በመጓዝ የሚያወጡትን  ወጪና ጊዜን እንደሚያስቀር አመልክተዋል።

ግንባታውን የሚያከናውነው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ  በጥራትና በታቀደለት ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚያበቃ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስትም ግንባታው ከግብ እንዲደርስ  ድጋፍ እንዲያደርግ  ጠይቀዋል።

አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፤ በክልሉ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ  መካሄዱ በአካባቢው የህክምና ቱሪዝምን ለመጀመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ  እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ሆስፒታሉም በጥራትና በታቀደለት ጊዜ  እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት የክትትልና የድጋፍ ስራዎችን እንደሚያከናውን አረጋግጠዋል።

የሀገር መከላከያ ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ሰለሞን ደመቀ፤ "በ3ሺ 200 ካሬ ሜትር ላይ ባለ ስምንት ወለል የሚይዘው የሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት የሚያከናውነው የሀገር መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ነው" ብለዋል።

ኢንተርፕራይዙም  ፕሮጀክቱን በተሰጠው ሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ  በጥራት ሰርቶ እንደሚያስረክብ አስታውቀዋል።

የፌዴራል ሐረር ፖሊስ ሆስፒታል በ1958 ዓ.ም እንደተመሰረተ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም