ቀጥታ፡

መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር በአካባቢው ሰላም ለማስፈን የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል- በምዕራብ ወለጋ ዞን ቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች

ሀምሌ 2/2014 /ኢዜአ/ መንግስት እያደረገላቸው ካለው ሰብዓዊ ድጋፍ በተጓዳኝ በአካባቢው ሰላም ለማስፈን የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቶሌ ቀበሌ በፈጸመው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ጠየቁ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎችን ከመደገፍ ባሻገር በአካባቢው በተጠናከረ መልኩ ህግ የማስከበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኢዜአ በስፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው ዜጎች እንዳሉት፤ የሽብር ቡድኑ በስፍራው በሰላማዊ ዜጎች ላይ እጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ፈጽሟል፡፡

የአርሶ አደሩን ቤትንና ንብረት በመዝረፍ የነዋሪዎችን የዕለት ጥሪት አሳጥቷል።

የሽብር ቡድኑ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ከፈጸመው ጭፍጨፋ የተረፉ ዜጎች እንደሚሉት፤  በደረሰባቸው ጥቃት ለከፍተኛ የስነ-ልቦና እና አካላዊ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ኃይሉ አካባቢውን ተቆጣጥሮ ህግ የማስከበር ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰብዓዊ ድጋፍም እየቀረበላቸው ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው የጠየቁት፡፡

መንግስት የጀመራቸው የዕለት ድጋፎች መልካም እንደሆኑ የተናገሩት ነዋሪዎቹ ተጎጂዎችን በዘላቂነት መቋቋም፣ የጸጥታ ጥበቃ፣ የእርሻ ግብዓት፣ የእለት ደራሽ የምግብና የአልባሳት ቁሳቁስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተለይ  የጸጥታ ስራው አሸባሪው ሸኔ ለአካባቢው ስጋት አለመሆኑ እስኪረጋገጥ  ድረስ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በአካባቢ ዘላቂ ሰላም ተረጋግጦ ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ ሁሉም ባላድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎችን ከመደገፍ ባሻገር በአካባቢው በተጠናከረ መልኩ ህግ የማስከበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በኮሚሽኑ በምዕራብ ወለጋ ዞን የክልሉ ልዩ ኃይል ዋና አዛዥ ኮማንደር ነገራ ዱፌራ የጸጥታ ኃይሉ አሸባሪ ቡድኑ ላይ እግር በእግር እየተከተለ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ አብራርተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም