የፎሬንሲክ ዲ.ኤን.ኤ ምርመራ በሀገር ውስጥ መጀመሩ የፖሊስ ወንጀል ምርመራ አቅምን አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
የፎሬንሲክ ዲ.ኤን.ኤ ምርመራ በሀገር ውስጥ መጀመሩ የፖሊስ ወንጀል ምርመራ አቅምን አሳድጓል
ሐምሌ 2 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፎሬንሲክ ዲ.ኤን.ኤ ምርመራ በሀገር ውስጥ መጀመሩ የፖሊስ ወንጀል ምርመራ አቅምን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤልአስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የግለሰቦችን ማንነት የሚለይ የፎረንሲክ ዲ ኤን ኤ ላብራቶሪ አገልግሎትን ዛሬ በይፋ አስጀምሯል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ወጪ በማውጣት አገልግሎቱን ከውጭ አገራት ስታገኝ መቆየቷም ነው የተገለጸው፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት፣ አገልግሎቱ የፖሊስ የምርመራ ስራን በማጎልበት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ የፖሊስ የምርመራ ስራ ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የጸዳ ለማድረግ እየተከናወነ ያለውን ስራ በብዙ መልኩ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ለፍትህ ስርዓቱ የተሻለ ማስረጃዎችን ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ኢትዮጵያ አገልግሎቱን በውጭ ሀገር ለማግኘት ታወጣው የነበረውን ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስቀርም ነው ያነሱት፡፡
በተጨማሪ አገልግሎቱ በፍርድ ቤት ለሚታዘዙ የምርመራ ስራዎች እንዲሁም ከቤተሰብ ጋር ተያይዞ ለሚቀርብ የዲኤን.ኤ ምርመራ ለመስጠት እንደሚያስችልም አብራርተዋል።
በአጠቃላይ አገልግሎቱ ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ተቋም ለመገንባት እያከነወነች ያለውን ስራ በማገዝ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተናገሩት፡፡
በኮሚሽኑ ፎሬንሲክ ምርመራ ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ከተማ ደባልቄ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ሀገር ውስጥ ባሉ መያተኞች የሚሸፈን መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪ ፖሊስ በቴክኖሎጂ ታግዞ ውጤታማ ስራ እንዲሰራ እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ይህም በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ የራሱን በጎ ሚና ያበረክታል ብለዋል።