መንግስት ያስቀመጠውን የሰላም አማራጭ ሁሉም ወገኖች ተግባራዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ያስቀመጠውን የሰላም አማራጭ ሁሉም ወገኖች ተግባራዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት ያስቀመጠውን የሰላም አማራጭ ሁሉም ወገኖች ተግባራዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች ገለጹ።
መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላም አማራጭ ለመፍታት መወሰኑን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህንን ስራ በዋናነት የሚያከናውንና ሰባት አባላትን የያዘ ቡድንም አቋቁሟል፡፡
የሰላም ሂደቱም ህገ-መንግስታዊ መርሆን ያከበረ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር የማያቀርብና ሂደቱም በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚመራ እንዲሆን አቋም መያዙን የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዴዮን ጢሞቲዮስ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
በመንግስት ውሳኔ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ የቀጣናው የሰላምና ደህንነት ጠበቃ መሆኗን አስታውሰዋል።
ዶክተር ሙላቱ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራትና ጎረቤቶቿም ከግጭት ይልቅ ሰላም እንደሚበጃቸው አቋሟን በማራመድ እንደምትታወቅ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ አሁን ያጋጠማትን ችግር በመፍታት ወደሰላም እንድትመለስ ማድረግ የግድ ነው ይላሉ።
ለዚህም መንግስት የሰላም አማራጭ ውሳኔውን ማሳለፉን አድንቀው፤ ለኢትዮጵያ ሰላም ከኢትዮጵያውያን ውጭ ማንም ነጋሪ እንደማያስፈልግ ነው ያነሱት።
የቀድም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ መንግስት የተከተለው የሰላም ውሳኔ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ጦርነት ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈላት የተናገሩት አቶ ኃይለማርያም፤ በጦርነት የሚሳተፍ የትኛውም አካል ከጦርነት ማትረፍ እንደማይችል አብራርተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ጦርነትና ግጭት ሊቆም እንደሚገባና ችግሮችን በሰላም መፍታት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ሰላምን በማስፈንም ህብረተሰቡን ከስጋትና ከጭንቀት ኑሮ እንዲሁም ሀገሪቱን ከተጨማሪ ጉዳት ማላቀቅ እንደሚገባም እንዲሁ።
የቀድሞ መሪዎቹ አክለውም፤ የቀጣናው ሀገራት፣ አፍሪካና ዓለም ኢትዮጵያ ለሰላምና ደህንነት ትልቅ ሚና እንደምታበረክት ያውቃሉ፤ ለዚህም ከእኛ ብዙ ነገር ይጠብቃሉ ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ያሉ ውሰጣዊ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ሰላሟን ማረጋገጥ ለነገ የሚተው ስራ እንዳልሆነም ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለቀጣናው፣ ለአፍሪካና ለዓለም ሰላምና ደህንነት ያላትን ሚና ማስቀጠል እንደሚገባ በመጥቀስ።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም ጠብመንጃን ወደ ጎን ትቶ በውይይት መፍታት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ለመትከል ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ሚና እንደሚጠበቅም ነው ያነሱት።