ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን ወንድማማችነትና አንድነትን በማጽናት የጠላትን ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሐምሌ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን ወንድማማችነትንና አንድነትን በማጽናት የጠላትን ሴራ ማክሸፍ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ተናገሩ።

የ1 ሺህ 443ኛው ኢድ አል አድሃ/አረፋ/ በዓል ሶላት ስነ- ስርዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል።

በስነ ስርዓቱ የተገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ሁሉን ነገር ማሳካት የሚቻለው አገር ሲኖር ነው ፤ለዚህ ደግሞ የሰላም መረጋገጥ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

ሰላም ከአካባቢ እንደሚጀምር ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ ለአገር ደህንነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያን ማደግ፣ መለወጥና ሰላም መሆን የማይፈልጉ ኃይሎች በብሄር እና በሃይማኖት ሽፋን ችግር እየፈጠሩ መሆኑን አንስተዋል።

ይህንን ችግር ለመቀልበስ በመተሳሰብ፣ በህብረትና በአንድነት መጓዝ እንደሚገባ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ሼህ ሁሴን አወል እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ራሷን ለመለወጥ በአፍሪካም ተምሳሌት ለመሆን የጀመረችው ግስጋሴ ጠላቶቿን እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን የጠላትን ሴራ በአግባቡ ሊገነዘብ ይገባል ያሉት ሼህ ሁሴን፤ እኛን ለመከፋፈል ለሚጥሩ አካላት ቀዳዳዎችን በመድፈን ማሳፈር ይገባል ብለዋል።

እያንዳንዱ ሰው የአካባቢውንና የአገሩን ሠላም መጠበቅ ላይ በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባም አክለዋል።

አገር ሠላም የሚሆነው በወንድማማችነት በህብረት መቆም ሲቻል መሆኑንም ተናግረዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መንሱር ጀማል በበኩላቸው አገርን ችግር ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ በርካታ አጀንዳዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ከሌለች ሁላችንም የለንም" ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ለሰላም መረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን ማበርከት እንደሚጠበቅበት አጽንኦት ሰጥተዋል።ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ጠንከር ያለ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ መንሱር፤ በአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ገጽታዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳርፉትን ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል። "አንድነታችን በማጠናከር የጠላትን ሴራ ማክሸፍ አለብን" ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም