ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለዓባይ ወንዝ ዘላቂ ፍሰት የምታካሂደውን የአካባቢ ጥበቃ ስራ የታችኛው ተፋሰስ አገራት በወጪ መጋራት ጭምር ሊደግፉ ይገባል

ሐምሌ 02 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለዓባይ ወንዝ ዘላቂ ፍሰት የምታካሂደውን የአካባቢ ጥበቃ ስራ የታችኛው ተፋሰስ አገራት በወጪ መጋራት ጭምር ሊደግፉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ገለጹ።

ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ለኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ጨምሮ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ለዓባይ ወንዝ ዘላቂ ፍሰት ዋስትና የሚሰጡ ናቸው።

የዓባይ ወንዝ ልማት በአንድ በኩል ኢትዮጵያ አፈሯን ከመሸርሸር በመጠበቅ ልማቷን ለማረጋገጥ፣ በሌላ በኩል የውሃ ሀብቷን ዘላቂ ፍሰት እንዲኖረው ማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል።

የታችኛው ተፋሰስ አገራት ግብፅና ሱዳን ግን የዓባይ ወንዝ ልማት ለጋራ ጥቅም እንደሆነ ዕውነታውን ቢገነዘቡም የኢትዮጵያ አፈር ይቀርብናል በሚል ስጋት የኢትዮጵያን ጥረት እየደገፉ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የኢትዮጵያ የውሃና የአፈር ጥበቃ ስራዎች ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ በማድረግ የአገልግሎት ዕድሜውን ለማራዘም ሚናቸው ጉልህ ነው ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ላይ የምታካሂደው የአካባቢ ጥበቃ ስራ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አውስተዋል።

በተቃራኒው የታችኛው ተፋሰስ አገራት ዛሬም የቅኝ ግዛት ውሎችን ገቢራዊ ለማድረግ እየታገሉ እንደሆነ ገልጸው፤ የአሁኑ ትውልድ ይህን ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ ፈጽሞ እንደማይቀበለው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለዓባይ ወንዝ ዘላቂ ፍሰት የምታካሂደውን የአካባቢ ጥበቃ ስራ የታችኛው ተፋሰስ አገራት በወጪ መጋራት ጭምር ሊደግፉ እንደሚገባም ነው ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የተናገሩት፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመላ አገሪቷ 12 የውሃ ተፋሰሶች ላይ ህዝብን በማስተባበር የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባም የጉለሌ ዕጽዋት ማዕከልን ጨምሮ የተለያዩ የአረንጓዴ አሻራ ስፍራዎች እንዳሉት ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በመዲናዋ ከአራት ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሰፊ ዕውቀት ማዕከል በመሆኑ ከችግኝ ተከላ ባሻገር የአረንጓዴ አሻራ ውጤታማነት እንዲሰምር የምርምር ስራዎቹን ማድረግ ቁልፍ ተልዕኮው ላይ እየሰራ ነው ብለዋል።

ከወራት በኋላ ግብፅ በምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ምርምር ጉባዔውም ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ዘርፍ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም