የሽብር ቡድኖችና ጽንፈኞች በንጹሃን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት በዘላቂነት ለመከላከል መንግስት በተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሽብር ቡድኖችና ጽንፈኞች በንጹሃን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት በዘላቂነት ለመከላከል መንግስት በተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው
ሐምሌ 02 ቀን 2014(ኢዜአ) የሽብር ቡድኖችና ጽንፈኞች በንጹሃን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት በዘላቂነት ለመከላከል መንግስት በተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ አስታወቁ።
ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የሆነ "የግራጫ ጦርነት" ውስጥ መሆኗን ተገንዘቦ ለሀገራዊ ድል በጋራ መቆም ብቸኛው አማራጭ መሆኑንም ተናግረዋል።አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በምእራብ ወለጋ በሰው ልጆች ላይ ሊፈጸም የማይገባው አስነዋሪ ጭፍጨፋ በንጹሀን ዜጎች ላይ መፈጸሙ ልብ ሰባሪ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በጽንፈኞችና በሽብር ቡድኖች የሚፈጸሙ ንጹሀን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ለመግታትና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የችግሩን ምንጭ መረዳት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ዋነኛ የችግሩ ምንጭም አብሮነት እንዲሸረሸርና ኢትዮጵያ እንድትኮስስ ታስቦ ለዘመናት ሲሸረብ የቆየ የፖለቲካ ሴራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የሚንዱ ስራዎች ለዓመታት መሰራታቸውንና በምትካቸው ፅንፈኝነት ሲዘራ መቆየቱን አስታውሰው ይህም ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሚስተዋለው የሰላም መደፍረስ ተራ የአገር ውስጥ ችግር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ልማት የማይሹ የውጭ ሀይሎች ስውር እጆች ያለበት መሆኑን መዘንጋት አይገባም ብለዋል።
የአድዋ ድል የአፍሪካ ሀገሮች ቅኝ ግዛት በቃን እንዲሉ ያስተማረ በመሆኑ ጥቅማቸው የተቋረጠባቸው አካላት ኢትዮጵያ ላይ ማቄማቸውን ማስታወስ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ለአፍሪካ ሀገሮች ዘብ መቆሟ ያልተዋጠላቸው ሀይሎች ከኋላቀርነት እንዳትላቀቅ፣ ከተመጽዋችነት እንዳትወጣና ቀና እንዳትል ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ላይ ሁሉን አቀፍ ጦርነት መከፈቱን ጠቅሰው የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን ዋነኛ መሳሪያ አድርገው እየተጠቀሙባቸው መሆኑን አንስተዋል።
ወቅቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የሚከናወንበት በመሆኑ ይህን በማደናቀፍ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትለማ ርብርብ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ተናግረዋል።
ጠላቶቻችን ሁሉንም አይነት አማራጭ በመጠቀም ኢትዮጵያን ለማዳከም እየሰሩ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት በቆሙባቸው ጊዜያት ሁሉ ፈተናዎቻቸውን በድል መወጣታቸውን አስታውሰው ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ማንበርከክ የሚቻለው የህዝቦቿን አንድነት በመሸርሸር ነው የሚል አቋም ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ነው ያሉት።
በዚህም በብሄርና ሀይማኖት በመከፋፈል የርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች ህዝብና መንግስትን ለመነጠል ያለ እንቅልፍ እንደሚሰሩ ገልጸው የመሪዎችን ንግግር ከአውድ ዉጭ እየተረጐሙም ጭምር ችግር ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ተናግረዋል።
ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ አንዳንድ አካላት ከአውድ ውጭ በመተርጎም ለጥፋት መቀስቀሻነት ሊጠቀሙበት መሞከራቸው ተገቢነት እንደሌለው አንስተዋል።
ሽብርተኝነትና የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን በከፍተኛ ደረጃ እየፈተኑ በመሆኑ በችግር ውስጥም ሆነን እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ መስራት የግድ ነው ብለዋል።
በተለይ የፀጥታ መዋቅሩን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ለመከፋፈልና ኢትዮጵያን ለማዳከም በርካታ ስራዎች ቢሰሩም የፀጥታ ሀይሉ ከኢትዮጵያዊነቱ ዝንፍ አልል ማለቱን ተናግረዋል።
ይህም ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያን የሚመስልና የሚመጥን የጸጥታ አካል ለመገንባት ታስቦ የተተገበረው ሪፎርም ስኬታማ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል::
መንግስት ለዴሞክራሲና ለሰላም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያን ለማፅናት የተቋማት ግንባታ ላይ አትኩሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ድል በጋራ መቆም ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ተገንዝበው እጅ ለእጅ በመያያዝ የዳገቱን ጉዞ በስኬት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ