1443ኛው የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል በተለያዩ ከተሞች በድምቀት እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
1443ኛው የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል በተለያዩ ከተሞች በድምቀት እየተከበረ ነው
ድሬዳዋ/አርባ ምንጭ/ ሐረር/ጂንካ ሐምሌ 2/2014 (ኢዜአ) 1443ኛው የኢድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል በድሬደዋ፣ በአርባ ምንጭና በጂንካ ከተሞች በደመቀ መንገድ እየተከበረ ነው።
በድሬዳዋ አየር መንገድ አካባቢ በሚገኘው የኢድ መስገጃ ሜዳ እየተከበረ በሚገኘው የአረፋ በአል ላይ በብዙ ሺህ የሚገመቱ የገጠርና የከተማ አስተዳሩ የሙስሊሙ ማህበረሰብ እየተሳተፈ ነው።
ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ፈጣሪን በሚያወድሱ ዝማሬዎች ታጅበው በኢድ መስገጃ የተሰባሰቡት የሙስሊሙ ማህበረሰብ በአሁን ሰዓት ታላቁን በዓል በፀሎት ስነ ስርዓት እያከበሩ ናቸው።
በበዓሉ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ወርሰሜ እና የካቢኔ አባላት፣ የየመስጂዶቹ ኢማሞች፣ ኡላማዎችና ሼኾች ተሳታፊ ሆነዋል።
የድሬደዋ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ መሐመድ አብደላ በራርቲ እና ከፍተኛ አመራሮች ለመላው ሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር ፣ የአንድነት እንዲሆን ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቱ ሼኽ መሐመድ በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳት ፣ የተራቆቱትን በማልበስ፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት እንዲሁም የታመሙትን በመጠየቅ ማክበር እንደሚገባ ነው የገለፁት።
ይበልጥኑ ህዝበ መስሊሙ አንድነቱን በመጠበቅ በአገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ላይ እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል ።
"ለበአሉ ብቻ ሳይሆን የመተዛዘን፣ የመረዳዳት ባህላችን ሁሌም መቀጠል ያለበት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
በበአሉ ላይ የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል ።
በተመሳሳይ በአርባምንጭ ከተማ ህዝበ ሙስልሙ የአረፋ በዓል በታላቁ ጃሚ መስጅድ አደባባይ እያከበረ ነው፡፡
ህዝበ ሙስልሙም ካለው ለደሃው በመስጠት፣ በፍቅርና በአንድነት የምያከብሩበት ነው፡፡
በተመሳሳይ 1443ኛው የኢድ አላድሃ /አረፋ/ በአል በሐረሪ ክልል በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ነው።
የክልሉን ርዕሰ መስተደድር አቶ ኦርዲን በድሪን ጨምሮ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በክልሉ በሚገኙ መስኪዶች በአሉን በሃይማኖታዊ ስነ ስርአት እያከበሩ ይገኛሉ።
የእምነቱ ተከታዮች በአሉን የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ የአገርን ሰላም እና አንድነት በሚያረጋግጡ ሁኔታ በዓሉን እያከበሩት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
1443ኛው ዒድ አል አድሐ /አረፋ/ በዓል በጂንካ ከተማም በደማቅ ስርዓት እየተከበረ ነው።
በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውና ህዝበ ሙስሊሙ በአንድነት ለፈጣሪ ፀሎት የሚያደርሱበት 1443ኛው የዓመተ-ሒጅራው የዒድ አል-አድሐ /ዐረፋ/ በዓል በጂንካ እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።