ባለፉት አራት ዓመታት በእግር ኳስ ልማት የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ ነበሩ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት አራት ዓመታት በእግር ኳስ ልማት የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ ነበሩ
ሐምሌ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) ባለፉት አራት ዓመታት በእግር ኳስ ልማት የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ ገለጹ።
የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ከተካሄደ አራት ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን ኮሚቴው በቆይታው ከፍተኛ ተግባር ማከናወኑ ተገልጿል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ ሥራ አስፈጻሚው ኃላፊነት ተረክቦ ወደ ሥራ ከገባ አንስቶ እንደ ሀገር የተፈጠሩ ችግሮችና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በእግር ኳሱ ላይ ተጽዕኖ አሳድረው ማለፉቸውን አስታውሰዋል።
ፌዴሬሽኑ በሂደት የገጠመውን ችግር በመቋቋም ተጨባጭ የእግር ኳስ ልማት ሥራዎች ማከናወኑንና ለስኬቱ ዋና መሰረት የስትራቴጂክ ጥናት በማሰራት ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።
በተለይም የፕሪሚየር ሊግ ውድድር አክሲዮን ማህበር በመመስረት ውድድሮች በማህበሩ እንዲመሩ መደረጉና ጨዋታዎች በሱፐር ስፖርት መተላለፍ መጀመራቸው ከፍተኛ ስኬት ነበር ብለዋል።
ይህ ተግባር ክለቦች ከፍ ያለ ገቢ እንዲያገኙ፣ ባለሙያዎች ደግሞ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲመቻችላቸው እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡
እንዲሁም ተጨዋቾች ራሳቸውን በተለያዩ ሀገራት ለሚገኙ መልማዮች እንዲያሳዩ ከፍተኛ እድል እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ዋናው ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ መቻሉና በተለያዩ የእድሜ እርከን የሚገኙ ታዳጊዎች በአህጉርና ዓለም አቀፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች ያሳዩት ብቃት በበጎ የሚነሳ መሆኑን ተናግረዋል።
የበጀት ችግር የፌዴሬሽኑ ፈተና ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው፤ ይህንኑ ለመቅረፍ ከበርካታ አጋር አካላት ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታ በመፍጠር የገቢ አቅሙን የማጠናከር ሥራ መሰራቱንም ነው የገለጹት።
ገቢ ከማሳደግ በተጨማሪ የፌዴሬሽኑን ሃብት በቁጠባ ለመጠቀም የተሰሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤት ማምጣታቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም የካፍ አካዳሚን የብሔራዊ ቡድኑ ማረፊያ በማድረግ ለሆቴል የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ማስቀረት መቻሉን ነው የገለጹት።
በፌዴሬሽኑ የቀድሞ አመራሮች ተጀምሮ የነበረውን የሕንጻ ግዥ ሂደት በማስቀጠልና ከፊፋ ጋር በመነጋገር አዲስ ሕንጻ መግዛት መቻሉ ለባለሙያዎች ምቹ የሥራ አካባቢ ለመፍጠር ማስቻሉን ነው ያነሱት።
ይህም ሆኖ ፌዴሬሽኑ ውስንነቶች እንደነበሩበት በተለይ የእግር ኳስ ክለቦችን አደረጃጀት በማዘመን ላይ በቀጣይ ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ ነው የገለጹት።