ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የስርዓተ-ምግብና የምግብ ዋስትና ግብ ለማሳካት እያደረገች ያለው ጥረት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው

ሐምሌ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የስርዓተ-ምግብና የምግብ ዋስትና ግብ ለማሳካት እያደረገች ያለው ጥረት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ እንደሚሆን የአፍሪካ ሕብረት የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳዮችና የማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ሚናታ ሳማቴ ሲዙማ ገለፁ።

ኮሚሽነሯ ይህንን ያሉት በአዲስ አበባ በተካሄደው የ2022 የአፍሪካ የስርዓተ-ምግብና የምግብ ዋስትና ዓመት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ ነው፡፡

የማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽንና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር የተዘጋጀ ነው።

የአፍሪካ ሕብረት በአጀንዳ 2063 አማካኝነት የአህጉሪቱን የጋራ መጻዒ እድል መልካም እንዲሆን የሚያስችሉ የጋራ ግቦችን ያስቀመጠ ሲሆን፤ የጋራ ግቦቹም የአፍሪካን እምቅ አቅም መጠቀም ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።

ከግቦቹ መካከል በአፍሪካ የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ ማድረግ አንዱ ቢሆንም አህጉሪቷ አሁንም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጠቃሽ ናት፡፡

የዓለም አቀፍ የተመጣጠነ ምግብ ሪፖርት እንደሚያሳየው በአፍሪካ 13 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑ ጨቅላ ሕጻናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ዝቅተኛ ክብደት እንዳላቸው ያመላክታል።

30 ነጥብ 7 የሚሆኑ ከ0 እስከ 5 ዓመት እድሜ ያላቸው ሕጻናት ደግሞ የቀነጨሩ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በአህጉሪቷ የተመጣጠነ ምግብ ችግርን ለመቀነስ ይቻል ዘንድ ዘንድሮ በተካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ዓመቱ የስርዓተ-ምግብና የምግብ ዋስትና ዓመት እንዲሆን ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

የአፍሪካ ሕብረት የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳዮችና የማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ሚናታ ሳማቴ ሲዙማ  ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ስርዓተ-ምግብና የምግብ ዋስትና ለማሳካት ያስቀመጠውን ግብ  ለማሳካት እያሳየች ያለውን ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በተለይ አገሪቱ በሰቆጣ ቃል-ኪዳን በስርዓተ- ምግብና የምግብ ዋስትና የሰራችው ሥራ ለሌሎች የሕብረቱ አባል ሀገራት በተምሳሌትነት ሊወሰድ የሚችል ልምድ መሆኑን ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የተመጣጠነ ምግብ እጥረትንና የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት ባለው ቁርጠኝነት በአገሪቱ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የልማት መስኮች አንዱ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም የፌደራል መንግሥት ለዚህ ትግበራ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ እንዲሁም ክልሎችም ይህንኑ የሚስተካከል ገንዘብ መድበው በትኩረት እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የ2022 የአፍሪካ ሕብረት የስርዓተ-ምግብ እና የምግብ ዋስትና ዓመትን በመጠቀም በአፍሪካ የሕጻናትን መቀንጨር ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሉን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም