የብሔራዊ ምርመራ ህዝባዊ የአቤቱታ ቅበላ ዘዴን ማካሄድ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የብሔራዊ ምርመራ ህዝባዊ የአቤቱታ ቅበላ ዘዴን ማካሄድ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
ሐምሌ 1/2014 (ኢዜአ)፡ የብሔራዊ ምርመራ ህዝባዊ የአቤቱታ ቅበላ ዘዴን ማካሄድ የሚያስችል አሰራር ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በዜጎች ሰብዓዊ መብቶች አካባበር ላይ ያተኮረውን የመጀመሪያው ብሔራዊ ሕዝባዊ ምርመራ በሐዋሳ ከተማ ማካሄዱን አስታወቀ።
የኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ብሔራዊ ሕዝባዊ ምርመራውን አስመልክተው ትናንት በሐዋሳ ከተማ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና ኮሚሽነር ራኬብ በመግለጫቸው እንዳሉት ብሔራዊ ሕዝባዊ ምርመራ ውስብስብና በተደጋጋሚ የሚደርስ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በጥልቀት ለመመርመርና መፍተሄ ለማፈላለግ አጋዥ ነው።
ኮሚሽኑ ህዝባዊ የአቤቱታ ቅበላ ዘዴን በሁሉም ክልሎች በማካሄድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የመጀመሪያ የሆነው የብሔራዊ ምርመራ ህዝባዊ የአቤቱታ ቅበላ መድረክ ከሰኔ 27 እስከ 30/2014 በሐዋሳ ማካሄዱን ገልጸዋል።
ህዝባዊ የአቤቱታ መድረኩ ግልጽና ህዝባዊ ተሳትፎ የሚደረግበት፣ የመብት ጥሰት የደረሰባቸው ተጎጂዎች፣ ምስክሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በአንድ መድረክ የሚገኙበትን የምርመራ ስልት የተከተለ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሐዋሳ ከተማ በተካሄደው ብሔራዊ ምርመራ ከአቤቱታ አቅራቢዎች በተነሱ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባባት ላይ የተደረሰ መሆኑን አመልክተዋል።
ዋና ኮሚሽነር ራኬብ አክለውም ''በመድረኩ አቤቱታቸውን ያቀረቡ አካላት ምንም አይነት የደህንነት ስጋት እንዳያጋጥማቸው ከመንግስት የሥራ ኃለፊዎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል'' ብለዋል።
ህዝባዊ የአቤቱታ መድረኩን በሁሉም ክልሎች በማካሄድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ አሰራር እንደሚዘረጋ አስታውቀዋል።
በኮሚሽኑ የሴቶችና ህጻናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በበኩላቸው ህዝባዊ አቤቱታ የመቀበል ዘዴው ኮሚሽኑ ከሚያከናውናቸው ከመደበኛ የክትትልና የምርመራ ስራ በተለየ ዘዴ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ውስብስብና በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በሁለት ወገን ያሉ አካላትን በአንድ ቦታ ማወያየት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
መድረኩ ለችግሩ መፍትሄ የሚሰጡ አካላትንም ያካተተ በመሆኑ ችግሮች ምላሽ እንዲያገኙ የሚያደርግና መሰረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶች በምንም ዓይነት ሁኔታ መጣስ እንደሌለባቸው ንቃተ ሂሊናን ለማዳበር የሚያግዝ መሆኑንም አብራርተዋል።፡
መድረኩ የተሳካ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሮቹ በመድረኩ ከጋሞ፣ወላይታ፣ደራሼ፣አማሮ፣ኮንሶ፣ጌዲኦና ጉራጌ አካባቢዎች ጥያቄዎች ተነስተው በሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
መንግስትን ጨምሮ በመድረኩ የተገኙ ሌሎች አካላትም በቀጣይ በተነሱ ችግሮች ዙሪያ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡና ኮሚሽኑም ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።