የኢትዮጵያ ህዝብ ደጀንነት ሰራዊቱ ለአገር ህልውና ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንዲሆን አድርጎታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ህዝብ ደጀንነት ሰራዊቱ ለአገር ህልውና ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንዲሆን አድርጎታል
ሐምሌ 1/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ ደጀንነት የመከላከያ ሰራዊቱ ለአገር ህልውና ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ የ8ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል ገለጹ፡፡
የመከላከያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣን ማንኛውም ጥቃት በብቃት መመከት የሚያስችል የሰራዊት አቅምና ትጥቅ መያዙንም ገልጸዋል፡፡
የ8ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሰራዊቱ የጀግንነትና የአሸናፊነት ሚስጥር የኢትዮጵያ ህዝብ የተሟላ ድጋፍ ነው፡፡
በዚህም አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመበት ወቅት ጠላትን በገባበት ሁሉ በማስቀረት የኢትዮጵያ አለኝታ መሆኑን አሳይቷል ብለዋል፡፡
የ8ኛ ዕዝም በህብረብሔራዊ ዘመቻ ወቅት ትዕዛዝና ስምሪት በወሰደበት ግንባር የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ በመግታት ታላቅ ጀብዱ ፈጽሟል ብልዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱ የአሸናፊነትና የአይበገሬነት ምንጩ ህዝቡ መሆኑን የገለጹት ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል፤ በጦርነቱ ወቅት የሚችለውን ሁሉ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የጦርነት ግንባር ድረስ በመዝለቅ ለሰራዊቱ ስንቅ አቅርቧል፤ ሚሊሻው ማረሻውን አስቀምጦ በውጊያ ተሰልፏል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ሰራዊት ማለት ህዝብ መሆኑን በተግባር አስመስክረዋል፤ አሁንም ድጋፉ ከጎናችን አልተለየም፤ ልጆቹንም ተዋጉ፣ ድንበር ጠብቁ ብሎ መርቆ ሰጥቶናል ነው ያሉት፡፡
የመከላከያ ሰራዊትም የሚተማመንበትን ህዝብ ደጀን በማድረግ ማንኛውንም የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ከህዝቡ ደጀንነት ባለፈ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘርን ጥቃት መመከት የሚያስችል ጠንካራ አደረጃጀት ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚዘምን የሰው ሀይልና በትጥቅ የዳበረ ሰራዊት ገንብተናል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰራዊቱ ያለውን ድጋፍና እምነት ጠንቅቀን እናውቃለን ያሉት ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል፤ ለደጀኑ ህዝባችን አስተማማኝ ምሽግ ሆነን እናገለግላለን ነው ያሉት፡፡
በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተደረገው ሪፎርም እኩልነትና ወንድማማችነት በማስፈን ለዜጎች ደህንነትና አገር ሉዓላዊነት መከበር ዋስትና የሚሆን ሰራዊት መገንባት ማስቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መናገራቸው ይታወሳል፡፡