ኀብረተሰቡ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የበኩሉን አሻራ ማሳረፍ ይጠበቅበታል

ሐምሌ 01 ቀን 2014(ኢዜአ) ኀብረተሰቡ በየአካባቢው በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት አሻራውን ማሳረፍ እንደሚጠበቅበት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ሰራተኞች ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሰራተኞች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆነውን የደም ልገሳ መርሓ ግብር አካሄዱ።

የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች በዚሁ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ቢሳተፍ አገር በብዙ መልኩ ታተርፋለች ብለዋል።

በመሆኑም ኀብረተሰቡ የክረምቱን ወቅት በበጎ ስራ ላይ በመሳተፍ እንዲያሳልፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጥቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ፤ ጽህፈት ቤቱ በክረምቱ ወቅት በተለያዩ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ ላይ እንደሚሳተፍ ገልጸዋል።

በዚህም የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች በደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንደሚሳተፉ ለአብነት አንስተዋል።

ጽህፈት ቤቱ ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ቃሉ ወረዳ የአቅመ ደካሞችን ቤት ያደሰ ሲሆን በዚህ ዓመት ደግሞ ምዕራብ አርሲ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች የቤት እድሳት ይደረጋል ነው ያሉት።

በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች በስፋት መሳተፋቸውንም ጠቅሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ዓለምጸሓይ ጳውሎስም እንዲሁ ''ደም መለገስ ትልቅ ዋጋ ያለው ስጦታ ነው'' ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደም መለገስን ጨምሮ በሌሎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።

የጽህፈት ቤቱ ሰራተኞች ደም ከመለገስ ባሻገር በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር እንደሚያካሂዱም ነው ያነሱት፡፡

ዜጎች በየጊዜው ደም በመለገስ ለወገኖቻቸው አለኝታ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ወርቁ ጓንጉል ናቸው።

በጽህፈት ቤቱ የኦዲት ዘርፍ ኃለፊ የሆኑት አቶ ሙሉነህ ንጉሴም በተለያዩ ምክንያት ደም የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች መታደግ ትልቅ ተግባር ነው ይላሉ።

ሰብዓዊነት የሚለካው አንዱ ለሌላው መኖር ሲችል መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ለወገኖቻችን በሚጠቅም በጎ ስራ መሳታፍ አለብን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም