ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች በይነ መንግስታት ኮሚቴ አባል ሆና ተመረጠች

ሐምሌ 01 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የባህል ቅርሶች በይነ መንግስታት ኮሚቴ አባል ሆና ተመረጠች።

የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ ኮንቬንሽን አባል አገራት ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከሰኔ 28 እስከ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በፓሪስ ተካሄዷል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች በይነ-መንግስታት ኮሚቴ አባል ሆና መመረጧን ኢዜአ ፓሪስ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ በአባልነቷ በዩኔስኮ ከሚመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ሚዛናዊነት፣ውበትና ብዝሃነት የሚያንጸባርቁ እንዲሆን ትሰራለች ሲል ኤምባሲው ገልጿል።

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 180 አገራት የተሳተፉ ሲሆን ጉበኤው በዓለም ላይ የሚገኙ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ላይ ያተኮረ ነበር።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌውና በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም