ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ታንዛንያ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ዙርያ ምክክር ተካሄደ

ሐምሌ 01 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ እና ታንዛንያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውንና የዜጎች አገልግሎትን በተመለከተ ምክክር ተካሄደ።

በታንዛንያ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከታንዛንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊብራታ ሙላሙላ እና ከታንዛንያ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ሃማድ ማሱን ጋር በሁለቱ ሀገራት ወቅታዊ ግንኙነት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ሽብሩ በዚህ ወቅት መንግስት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት በማስቆም ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የተለያዩ ርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን አብራርተዋል።

የሁለቱ አገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የፖለቲካ ምክክር ማስጀመር መፋጠን እንዳለበት ፣ ወደ ታንዛኒያ ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያን የቪዛ አሰጣጥን በተመለከተ ሀሳባቸውን አንስተዋል።

በህገ ወጥ መንገድ በኬንያ ታንዛኒያ አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ ሲሞክሩ በታንዛኒያ የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን የኢትዮጵያ መንግስት ወደ አገራቸው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለመመለስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንዳለም ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የታንዛንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊብራታ ሙላሙላ በበኩላቸው የሁለቱ አገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የፖለቲካ ምክክር በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስጀመር ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ በህገ ወጥ መንገድ በኬንያ ታንዛኒያ አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ ሲሞክሩ በታንዛኒያ የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን የኢትዮጵያ መንግስት ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

የታንዛንያ የሀገር ውስጥ ሚኒስትሩ ሃማድ ማሱን በበኩላቸው ወደ ታንዛኒያ ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያን የቪዛ አሰጣጥን (የሪፈራል ቪዛን) በተመለከተ እየተሰራበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ከሁለትዮሽ ጉዳዮች ባለፈ በቀጣናዊ ጉዳዮችም መወያየታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም