ሠራዊቱ በልማት ስራዎች ላይ ያለው ተሳትፎ ለሀገር ያለውን ፍቅርና ክብር የሚያሳይ ነው- አቶ ርስቱ ይርዳው - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ በልማት ስራዎች ላይ ያለው ተሳትፎ ለሀገር ያለውን ፍቅርና ክብር የሚያሳይ ነው- አቶ ርስቱ ይርዳው

ሐዋሳ፤ ሰኔ 30/2014 (ኢዜአ) የመከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ በልማት ሥራዎች በንቃት በመሳተፍ እያከናወነ ያለው ተግባር ለሀገር ያለውን ክብርና ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ተናገሩ።
የደቡብ ክልልና የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በብላቴ የኮማንዶና አየር ወለድ ሃይል ማሰልጠኛ ማዕከል ዛሬ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ አከናውነዋል።
በችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓቱ ላይ አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት መከላከያ ሠራዊት ለሀገር ሉዓላዊነትና ለህዝብ ሰላም ሲል እየከፈለ ካለው አብይ ተልዕኮ በተጓዳኝ በልማት ስራዎች በመሳተፍ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።

መከላከያ ሠራዊቱ የሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት የማስከበር ስራዎቹ ባለፈ በውጪ በሚሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ስራዎች ሀገርን ያኮራ አመርቂ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በተለያዩ የልማት ስራዎች በንቃት በመሳተፍ አቅመ ደካሞችን የማገዝና የመደገፍ ተግባራቱ በሀገር ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ከሀገር ውጭም በችግኝ ተከላ በግብርና ስራዎችና ሌሎች ተግበራት አኩሪ ተግባር ማከናወኑን ገልጸዋል።
''በህይወታቸው፣ በደማቸውና በጉልበታቸው እያከናወኑ ያሉት የሀገራቸው ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የማድረግ ስራ ያኮራናል'' ብለዋል።
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የመከላከያ ሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን በማዕከሉ የደቡብ ክልል ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ ልዩ ኮማንዶ ሰልጣኞች በጋራ መሳተፋቸው እንዳስደሰታቸው አቶ ርስቱ ጠቁመዋል።
ማሰልጠኛ ማዕከሉ ከዋና ተግባሩ በተጓዳኝ የክልሉን ልዩ ሃይል በማሰልጠን እያደረገ ላለው ተግባርም ምስጋና አቅርበዋል።
የብላቴ የኮማንዶና አየር ወለድ ሃይል ማሰልጠኛ አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ በበኩላቸው መከላከያ ሠራዊቱ ጸረ ህዝብ ሃይሎች እያደረጉት ያለውን አፍራሽ ተግባር ለመመከት እየከፈለ ካለው የህይወት መስዋዕትነት ባለፈ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
''ህዝብ በሚሰራው ስራ ላይ በመሳተፍና ነገ ውጤቱን ስናይ በጣም ደስ ያሰኛል'' ያሉት ኮሎኔል ቦጃ፤ ከዚህ በተጓዳኝ በአካባቢው ያሉ ባለሀብቶችንና ነዋሪውን ህዝብ በማገዝና ሰላም በማስከበር ስራ ላይም በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በተከላ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከተሳተፉ የማዕከሉ ሰልጣኞች መካከል መሰረታዊ ወታደር ሀዋ መሀመድ በችግኝ ተከላው መርሐ ግብሩ በመሳተፏ ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።
ሌላው መሠረታዊ ወታደር መኳንንት አማረ በበኩሉ ከስልጠናው ባሻገር በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ መሳተፍ በመቻላቸው መደሰታቸውን ተናግሯል።
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ የደቡብ ክልልና የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣የማዕከሉ አዛዦች፣ አሰልጣኞች፣ ሰልጣኞችና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተሳትፈዋል።