ቢሮው የክልሉ አርብቶ አደሮች ግመሎቻቸውን ገዳይ ከሆነ መርዛማ ቅጠል እንዲጠብቁ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ቢሮው የክልሉ አርብቶ አደሮች ግመሎቻቸውን ገዳይ ከሆነ መርዛማ ቅጠል እንዲጠብቁ አሳሰበ

ጂግጅጋ ፤ ሰኔ 30/2014(ኢዜአ) በድርቅ ምክንያት ለእንስሳት ሳርና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሱ የክልሉ አርብቶ አደሮች ግመሎቻቸውን ገዳይ ከሆነ መርዛማ ቅጠል መጠበቅ እንዳለባቸው የሶማሌ ክልል እንስሳትና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ አሳሰበ።
በጅግጅጋ አካባቢ ከሌላ ወረዳ የመጡ 160 ግመሎች ሰሞኑን መርዛማ የዛፍ ቅጠል ተመግበው መሞታቸው በቤተ-ሙከራ (በላብራቶሪ) ምርመራ መረጋገጡን ቢሮው ገልጿል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር መሐመድ ገዓል ለኢዜአ እንዳሉት፤ ግመሎቹ ከሀርሺን ወረዳ በድርቅ ምክንያት የእንስሳት መኖ ለማግኘት በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ ቀበሌዎች የተሰባሰቡ የአራት አርብቶ አደር ቤተሰቦች ሀብት ናቸው ።
ግመሎቹን ለሞት ያበቃቸው መርዛማ ዛፍ በጉርሱም ወረዳና ጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ በአነስተኛ መጠን የሚገኝ መሆኑን ገልጸው፤ በአካባቢው መጠሪያ "በረከቴ" በመባል እንደሚታወቅ ጠቅሰዋል።
ቢሮው ከክልሉ የእንስሳት በሽታዎች መመርመሪያ ቤተ-ሙከራ (ላብራቶሪ) ባለሙያዎች ከሞቱት ግመሎች ናሙና በመውሰድ ምርመራ ማድረጉን ገልጸዋል።
በምርመራው ውጤት መሰረት ግመሎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው የዛፉን ቅጠል መመገባቸውና የእንስሳቱን የውስጥ አካላት እንደጎዳ መረጋገጡን አስረድተዋል።
በዚሁ መርዛማ የዛፍ ቅጠል ተመግበው የተመረዙ ግመሎች ፈጥነው ለቢሮው ባለሙያዎች ጥቆማ ባለማድረሱ ምክንያት ዛፉን ከተመገቡ 220 ግመሎች መካከል 60ዎቹ ብቻ ማዳን ሲቻል ቀሪዎቹ መሞታቸውን አስታውቀዋል።
ዛፉ በሚገኘባቸው አካባቢዎች የፀረ መርዛማ መድኃኒት በእንስሳት ጤና ኬላዎች በስፋት ለማቅረብና ህብረተሰቡም መከላከል እንዲችል ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር መሐመድ ገልጸዋል።
በጅግጅጋ ዙሪያ ከፊል አርብቶ አደሮች የሚያረቡት ግመል ሳይሆን የቀንድ ከብትና ፍየል በመሆኑና እነዚህ እንስሳት ቅጠሉን ስለተላሙዱት የደረሰባቸው ጉዳት እንደሌለ አመልክተዋል።
አርብቶ አደሩ ሳርና ውሃ ፍለጋ እንስሳሰቱ ይዞ ከቦታ ቦታ ከመንቀሳቀሱ በፊት ስለሚሄዳባቸው አካባቢዎች መረጃ ኖሮት እንስሳቱ መመገብ ያለባቸውን ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በክልሉ አብዛኛውን አካባቢ እስከ አሁን የቀጠለው ድርቅ ምክንያት ወደ ተራራማ አካባቢ የቤት እንስሳቶቻቸውን ይዞ የሚመጡ አርብቶ አደሮች ገዳይ ከሆነው መርዛማው ቅጠል ግመሎቻቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
እንዲሁም ችግሩ ግመሎቻቸውም ሆነ በሌሎች የቤት እንሳሳትን በሚያጋጥምበት ጊዜ ፈጥነው በአቅራቢያቸው ለሚገኙ የእንሰሳት ጤና ክሊኒክና ለቢሮው እንዲሁም ባለሙያዎች በማሳወቅ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ከጉዳት መታደግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል
ከአርብቶ አደሮች መካካል አቶ መሀሙድ ሙሴ በሰጡት አስተያየት ፤ በፋፈን ዞን ሀርሺን ወረዳ በተከሰተው ዝናብ እጥረት ምክንያት ግመሎቻቸውን ህይወት ለማቆየት ወደ ጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር መምጣታቸውን ገልጸው፤ ግመሎቹ የበሉት ዛፍ ቅጠል መርዛማ መሆኑን እንደማያውቁ ተናግረዋል ።
ግመሎቹ ዛፉን ቅጠል ከተመገቡ በኋላ ወዲያው ሆዳቸው ተነፍቶና አቅም እጥተው ይወድቃሉ ያሉት አርብቶ አደሩ፤ የሞቶባቸው ግመሎች እንዳሉ ገልጸዋል።
በሶማሌ ክልል በድርቁ ምክንያቶች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን እንስሳት መሞታቸውን ከክልል እንስሳትና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ገለጻ መረዳት ተችሏል።