ቀጥታ፡

በአሁኑ ጊዜ 105 የመንገድ ፕሮጀክቶች በዲዛይንና በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛሉ

ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሁኑ ጊዜ 105 የመንገድ ፕሮጀክቶች በዲዛይንና በጨረታ ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤  ከሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰተዋል።

ከመሰረተ ልማት ግንባታ አንፃር ለተነሳላቸው ጥያቄ በተለይም በመንገድ ዘርፍ የተጀመሩ የግንባታ ስራዎችን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በፌደራል መንግስት ከሚከናወኑት 331 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል 226 የሚሆኑት ብቻ 379 ቢሊዮን ብር ፋይናንስ እንደሚደረግባቸው አንስተዋል።

በሀገሪቱ በጥቅሉ ከ49 በላይ ከባድ ጥገና የሚያስፈልጋቸው መንገዶች በመኖራቸው እድሳት እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ 105 የመንገድ ፕሮጀክቶች በዲዛይንና በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ አንስተው የዲዛይንና የጨረታ ስራ አልቆላቸው በወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት ብቻ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸውም ተናግረዋል።

ለአብነት ከአልበርኮቴ እስከ መተሀራ ሀረር አካባቢ እየተሰራ ያለው መንገድ ከ7 ዓመት በፊት የተጀመረና በወሰን ማስከበር ችግር ስራው ተጓቶ የነበረ ስለመሆኑ አንስተዋል።

አሁን ላይ ችግሩ ተፈቶ ወደ ስራ መግባቱን ገልፀዋል መንገዱን በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከድሬዳዋ ጎዴ 220 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው መንገድ በተያዘለተ ጊዜ ለመስራት ጥረት እንደሚደረግ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንዶች አስተዳደር የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ እየሰራ ሰለመሆኑ ጠቁመዋል።

ከመንገድ ፕሮጀክቶች አንፃር ቀድመው የተባላሹ መንገዶችን እያስተካከሉ የተጀመሩ መንገዶችን የማፋጠን ስራ እንደሚከናወን አፅኖት ሰተዋል።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትን በተመለከተ ሃይል ማመንጨት፣ የመነጨውን ሃይል ማስተላለፍ፤ የተላለፈውን ሃይል ማከፈፋፈል፤ የተከፋፈለውን ሃይል ማሰራጨት የተባሉ አራት መሰረታዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ከተመረተው የኤሌክትሪክ ሃይል በማስተላለፍ ስርዓት ውስንነት ብቻ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው ለብክነት እንደሚዳረግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያለው አጠቃላይ 110 ሺህ ኪሎ ሜትር የኢሌክትሪክ ሃይል ማሰራጫ መስመር ቢኖርም አብዛኛው ጥገና የሚሻ በመሆኑ ሃይል እየባከነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በማምረት፣ በማስተላለፍ፣ በማከፋፈልና በማሰራጨት ረገድ ሰፊ ሀብት ፈሰስ ተደርጎ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የያዘችውን የኤሌክትሪክ ሃይልፕሮጀክቶች ስታጠናቅቅ በምርት ብቻ አሁን ከምታገኘው እጥፍ የሀይል ምርት እንደምታገኝም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም