አሸባሪው ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተሰለፈ የህዝብ ጠላት በመሆኑ በጋራ ታግለን ማጥፋት አለብን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተሰለፈ የህዝብ ጠላት በመሆኑ በጋራ ታግለን ማጥፋት አለብን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተሰለፈ የህዝብ ጠላት በመሆኑ በጋራ ታግለን ማጥፋት አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
የምክር ቤት አባላት ከአሸባሪው ህወሃት ጋር መንግስት የሚያካሂደው የሰላም ውይይት፣ አሸባሪው ሸኔ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈፀመው ስላለው ጭፍጨፋ እና ሌሎችም ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ሸኔም ሆነ ሌሎች አሸባሪዎች አገርና ህዝብን ለማፍረስ የተሰለፉ የጋራ ጠላቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአሸባሪው ሸኔ የሽብር ተግባር በህዝብ ላይ ያነጣጠረ እንጂ በአንድ ብሔር ላይ ብቻ ያነጣጠረ አድርጎ መመልከት ትክክል አለመሆኑንም አስረድተዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ጠላት ሆነው የተነሱ አሸባሪዎችን ለማጥፋት መንግስት ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰው፤ የህዝቡ የተጠናከረ ትብብር እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የሸኔ አሸባሪ ቡድን የኦሮሞም ሆነ የማናችንም የጋራ ጠላት መሆኑን ጠቅሰው፤ "አባቱን አስሮ የሚያቃጥል አሸባሪ ለማንም የማይመልስ የህዝብ ጠላት እንጂ የማንም ወዳጅ ሊሆን አይችልም" ብለዋል።
አሸባሪው ሸኔ በኦሮሚያ የተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች በርካታ አመራሮችን በመግደል ጭምር አገር ለማፍረስ እየሰራ ያለ ቡድን መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በርካታ የጸጥታ ኃይሎች ለአገርና ለህዝባቸው ሲሉ ከአሸባሪዎች ጋር በመዋጋት ውድ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ጠቅሰው ለዚህም ውለታቸው ተገቢውን ክብር መስጠት አለብን ብለዋል።