በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎችን ስነምግባር ለማሻሻል እንሰራለን- መምህራንና ወላጆች - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎችን ስነምግባር ለማሻሻል እንሰራለን- መምህራንና ወላጆች
በአዲሱ የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ስነምግባር በማሻሻል ሀገራዊ ስሜትና መልካም ስነምግባር ያለው ትውልድ ለማፍራት እንደሚሰሩ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ወላጆች ተናገሩ፡፡ በኒው ኤራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመምህራን ልማት ምክትል ርዕሰ መምህር ሀይሉ ታደሰ እንደገለጹት በ2010 ትምህርት ዘመን በመጤ ባህል ድርጊት ላይ የተሳተፉ ተማሪዎችን በመምከር ከትምህርታቸው እንዳይዘናጉ ማድረግ ተችሏል። የትምህርት ጥራት ማጋገጥ የሚቻለው ስነ ምግባር ሲሻሻል ብቻ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መምህሩ በአዲሱ ትምህርት ዘመን በስነ-ምግባር በተለይም መጤ የባህል ወረርሽኝን ለመከላከል በተጠናከረ መልኩ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። የመማር ማስተማር ስራዎችን በቅንጅት ለመስራት በመስከረም ወር መጨረሻ ትምህርት ቤቱ ከመምህራንና ወላጆች ጋር የመጀመሪያ ጉባኤ እንደሚያካሄድም ነው የገለጹት። ሌላው አስተያየት ሰጪ የአጸ ፋስል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስነዜጋና ስነ ምግባር መምህርት አበባው ሳልለው በስነምግባር የታነጸ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት ለ2011 የትምህርት ዘመን ዝግጁ መሆናቸውን ነው ያብራሩት። በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ፓርላማ ተቋቁሞ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር እና በሌሎችም ክበባት ተማሪዎችን በማሳተፍ የሀገር ሀላፊነትን አውቀው እንዲያድጉ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡ የዚሁ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር ቸርነት ዳባ እንደተናገሩት በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎችን ስነ ምግባር ለማሻሻልና ጥራትን ለማምጣት ከወላጆች፣ ከመምህራንና ከተማሪዎች ጋር ተወያይተው ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አሳውቀዋል። የተማሪዎችን ስነ ምግባር ለማሻሻል መምህራን ብቻ ሃላፊነቱን የሚወጡት ባለመሆኑ ህብረተሰቡ በጋራ መሥራት እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ትምህርት በእውቀት፣ በክህሎትና በጥበብ የተካነ እና በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት መሆኑን የተናገሩት የቤተልሄም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ሴይፈ ስለሺ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከወላጆ ጋር በጋራ በመስራት ተማሪዎችን በመሸለምና በማበረታታት የተሻለ ልምድ ነበረን ነው ያሉት። በአዲሱ የትምህርት ዘመንም ልምዱን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ከመምህራን፤ ወላጆችና ተማሪዎች ጋር ውይይት አድርገው የሶስትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል፡፡ የቤቴልሔም ትምህርት ቤት ተማሪ ወላጅ አቶ መኮንን ገብረማሪያም በበኩላቸው ተገቢ ያልሆ ተግባርን ለመከላከልና የሀገር ፍቅር ያለውን ትውልድ ለማፍራት ከትምርት ቤቱ ጋር ያደረጉት ስምምነት እዳንስደሰታቸውና በቅርበት ለመስራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌላዋ ወላጅ ወይዘሮ አበበች በቀለ እንዳሉት በተማሪዎቹ አለባበስ፣ ጸጉር አያያዝና ሌሎች የስነ-ምግባር ጉዳዮች ላይ ከትምህርት ቤቱ ጋር በጥምረት ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በስምምነቱ መሰረትም ስነ-ምግባርን የተላበሰ ትውልድ ለማፍራት የወላጅነት ሃላፊነታቸውን እንደምወጡም አስታውቀዋል፡፡