ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ወንድማማችነትን የሚነጣጥሉ ተግባራትን እየነቀለች ብልጽግናዋን እያረጋገጠች ነው- ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

ሐረር፤ ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የሚከፋፍሉና ወንድማማችነትን የሚነጣጥሉ ተግባራትን እየነቀለች ብልጽግናዋን እያረጋገጠች ትገኛለች ሲሉ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ተናገሩ።

የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የጸጥታ አካላት የተሳተፉበት  የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ተካሄዷል።

በመረሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት   በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ፤ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የለውጥ መንገዶችን እየተከለች የሚከፋፍሉና ወንድማማችነትን የሚነጣጥሉ ተግባራትን በመንቀል  ብልጽግናዋን እያረጋገጠች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ዛሬ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት፣የፌዴራልና የክልሉ ፖሊስ አባላት፣ ሚሊሻና ደንብ አስከባሪዎች ያከናወኑት የችግኝ ተከላ የጸጥታ አካሉ ለአንድ ዓላማ መቆማቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ይህም ለመልካም ተግባራት፣ተልዕኮና ግብ በጋራ መቆማቸውን ለሌሎች በግልጽ የሚያሳይ በመሆኑ  ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የሚገኙ የጸጥታ አካላት የህብረተሰቡን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየሰሩ ነው።

የጸጥታ አካሉ በሚያከናውነው የተቀናጀ የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራ  የህብረተሰቡ ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዲገኝ አስችሏል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚከናወነው የልማት ስራ የጸጥታ አካሉ ከክልሉ መንግስት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በክልሉ በተለይ ዘንድሮ እየተከናወነ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጡ የፍራፍሬ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ችግኙ ውጤታማ እንዲሆን የመንከባከቡ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስበዋል።

በቀጣይም የክልሉ መንግስትና ህብረተሰቡ የጀመሩትን የልማት እና የሰላም ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ኦርዲን አረጋግጠዋል።

አካባቢን ከበረሃማነት ለመከላከል  ሁላችንም ለአረንጓዴ ልማት በትኩረት መስራት አለብን ያሉት ደግሞ  የምስራቅ ዕዝ የዙሪያ ጥበቃ ሃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ዳኘው አዲስ ናቸው።

ሰራዊቱም  የኢትዮጵያን ሰላም እና ልማቱን እያረጋገጠ ለትውልድ  አሻራውን ያኖራል ሲሉ ገልጸዋል።

የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ነስሪ ዘከርያ በበኩላቸው፤  የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ በሀገሪቱ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አንስተው፤ ይህንን ተግባር በክልሉ አጠናክሮ ለማስቀጠል የፖሊስ አባላቱ አስፈላጊውን ስራ እንደሚያከናውኑ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም