የትኛውንም አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት በመንግስት የተጀመረው ጠንካራ እርምጃ ይቀጥላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የትኛውንም አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት በመንግስት የተጀመረው ጠንካራ እርምጃ ይቀጥላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የትኛውንም አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት በመንግስት የተጀመረው የተቀናጀ እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።
አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች በአሸባሪዎች ታስቦ የነበረ የጥፋት እቅድ መክሸፉንም ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6ኛው ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
የምክር ቤቱ አባላት ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል።
አሸባሪው ሸኔ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈፀመው ስላለው ጭፍጨፋ የመንግስት ህግ የማስከበር እርምጃ ምን እንደሚመስል ከምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ በምላሽና ማብራሪያቸው በኢትዮጵያ የትኛውም የአሸባሪ ቡድን በመንግስት በተጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ይጠፋል ብለዋል።
የጸጥታ ሃይሎች አሸባሪዎችን ለማጥፋት ለሚወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ትግልና የህይወት መስዋእትነት እየከፈሉ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
አሸባሪነት የዓለም ስጋት ሆኖ መቀጠሉን ጠቅሰው በኢትዮጵያም ይሄው ችግር የተለያዩ ጥፋቶችን እያስከተለ በመሆኑ አሸባሪዎችን ለማጥፋት የተጀመረው ጠንካራ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአሸባሪዎች እኩይ ዓላማ እና እቅዶች አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የጥፋት ውጥናቸው እንዲከሽፍ ተደርጓል ብለዋል።
መንግስት የዜጎችን ሰላም ማስከበር ዋነኛ ተግባሩ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዙሪያ ለሚደረጉ ጥረቶች የህዝቡ ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት አሸባሪዎችን እየተፋለመ በርካታ ጥፋቶችን ቀድሞ በመቆጣጠር መከላከል መቻሉን ተናግረው አሸባሪዎችን ለማጥፋት የህዝቡን የተጠናከረ ትብብር ጠይቀዋል።