የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሰረተ ልማቶች ለአገልግሎት በቁ - ኢዜአ አማርኛ
የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሰረተ ልማቶች ለአገልግሎት በቁ
ጎባ ሰኔ 30 ቀን 2014(ኢዜአ)--- በምስራቅ ባሌ ዞን ከ170 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡና የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሰረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።
ከተመረቁት የልማት ፕሮጄክቶች መካከል በወረዳዎቹ የተገነቡ የመጠጥ ውኃ ፕሮጄክት፤ የቡኡረ ቦሩ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት፤ የአርብቶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከልና የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይገኙበታል።
በዞኑ ሰዌናና ራይቱ የአርብቶ አደር ወረዳዎች ውስጥ ከ170 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡት የልማት ፕሮጄክቶቹ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡
በሁለቱም የአርብቶ አደር ወረዳዎች ውስጥ የተገነቡት የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጄክቶች በተለይ ህብረተሰቡ የመጠጥ ውኃ ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርገውን እንግልት እንደሚያስቀር ታምኖበታል።
የአርብቶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከሉም አርብቶ አደሩ በቅርበት ከዘመናዊ የግብርና አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲተዋወቅና የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ እገዛ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡
ፕሮጄክቶቹን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እሸቱ በቀለ በወቅቱ እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በመመለስ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡
በተለይ በዞኑ ለአገልግሎት የበቁት የልማት ፕሮጄክቶች በልማት ወደ ኋላ ቀርቶ የነበረውን የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ለማነቃቃት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ነው የገለጹት፡፡
አቶ እሸቱ እንዳሉት መንግስት በቀጣይም ህዝቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በመለየት በአጭርና ረዥም ጊዜ ዕቅድ ተደራሽ ማድረጉን እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡
አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረጉ እነዚሁ የልማት ፕሮጄክቶች በዘላቂነት የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጡ ህዝቡ ሊንከባከባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው የክልሉ መንግስት የተለያዩ ተግዳሮቶችን በመቋቋም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያደረገ የሚገኘው ጥረት እንዲሰምር የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላሙን በመጠበቅ ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
ከሰዌና ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ማህሙድ አብደላ በሰጡት አስተያየት የመጠጥ ውኃን በአካባቢያቸው በማግኘት ንጹህ ውኃን ለመፈለግ ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እንደሚያስቀር ተናግረዋል፡፡
ንጽህናው ያልተጠበቀ ውኃ በመጠጣት ይደርስባቸው ከነበረው በሽታ እንጠበቃለን የሚል እምነት መያዛቸውንም ተናግረዋል፡፡
"በአካባቢያችን የተገነባውን ትምህርት ቤት በአግባቡ በመያዝ ልጆቻችንን አስተምረንበት ለቁምነገር በማብቃት ድርሻችንን እንወጣለን" ያሉት ደግሞ የራይቱ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሀሰን ጉቱ ናቸው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከሰኔ 20 እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ከ20 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት የማብቃቱ ሥነ-ሥርዓት እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡