የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የተፋሰስ ልማት ለታችኛው የዓባይ ተፋሰስና ለጎረቤት ሀገራትም በረከት ይዞ መጥቷል- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የተፋሰስ ልማት ለታችኛው የዓባይ ተፋሰስና ለጎረቤት ሀገራትም በረከት ይዞ መጥቷል- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር
ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የተፋሰስ ልማት ለታችኛው የዓባይ ተፋሰስና ለጎረቤት ሀገራት በረከት ይዞ መምጣቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ ተናገሩ።
ዓለም ላይ ከኮቪድ ወረርሽኝና ከግጭት ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ ትልቅ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው።
ግጭትና የአየር ንብረት ለውጥ ግንኙነት እንዳላቸው የሚያነሱት የዘርፉ ተመራማሪዎች በአየር ንብረት ለውጥ በሚከሰት ድርቅ ምክንያት የተፈጥሮ ሀብትን መጠቀም ባለመቻሉ የሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ግጭትን እንደሚያባብስ ይጠቅሳሉ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራ ላይ በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።
በተለያየ ጊዜ የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ፣የእርከን ስራና የተፋፈስ ልማት ስራዎች በውሃ ሃብት ልማት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለታችኛው የዓባይ ተፋሰስና ለሌሎችም ጎረቤት ሀገራት በረከት ይዞ መምጣቱን በመግለፅ።
የአረንጓዴ አሻራው በኢትዮጵያ የሚገኙ ምንጮች እንዲጎለብቱ፣ ድርቅን ለመቋቋም የሚያስችል አረንጓዴ ምህዳር እንዲፈጠር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ገባሮች እንዲጠናከሩ እያደረገ መሆኑን በማሳያነት በመጥቀስ።
ይሁን እንጂ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የኢትዮጵያን ጥረት በአዎንታ ከመመልከት ይልቅ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠቀም የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ ይሞክራሉ።
የሴራቸው ዋነኛ መነሻ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በመጠቀም ድህነትን በማስወገድ የዜጎቿን ህይወት ታሻሽላለች ከሚል የኢትዮጵያን ከፍታ ካለመፈለግ የመነጨ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እየገነባች ያለችው የዓባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብቷን ሌሎች ሀገራትን በማይጎዳ መልኩ ተግባራዊ በማድረግ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የዓባይ ወንዝን በተመለከተ ሌሎች ሀገራት የወንዝ የውሃ መጠን መቀነስ ወይም በሃይድሮሎጂካል መንገድ የሚከሰት ድርቅ መነሻዎች ላይ የተዛባ አመክንዮ እንደሚሰነዘሩ ተናግረዋል።
የወንዝ የውሃ መጠን መቀነስ የሚከሰተው በአየር ንብረት ለውጥ ወይም በዝናብ መቀነስ እንደሆነ ሀገራቱ ሊገነዘቡ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።የዝናብ መቀነስ ደግም በኢትዮጵያ እጅ ላይ ያለ ሰው ሰራሽ ጉዳይ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ክስተት መሆኑ ላይ በመግባባት በድርቅ ላይ ያላቸውን የተዛባ አቋም መቀየር አለባቸው ብለዋል።
ሀገራቱ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰተውን ድርቅና የወንዞች የውሃ መጠን መቀነስን በአግባቡ በመረዳት በጋራ መስራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ኢትዮጵያ ዓባይን ጨምሮ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የምታካሂደው የልማት ስራ ወንዞችን በመንከባከብና ሌሎችን ሀገራት በማይጎዳ መልኩ መሆኑን ማወቅ አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ለህዝባዊ ጥቅም ስታለማ እውነታውን ለዓለም በመግለጽ እንጂ በድብቅ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያንም ወንዞቻቸው እንዳይደርቁ በአረንጓዴ አሻራና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እያደረጉ ላሉት ትጋት በምላሹ የተፈጥሮ ሀብታቸውን በመጠቀም የመልማት መብት አላቸው ነው ያሉት።
በርካታ ስራ አጥ ወጣት ባለባት ሀገር ኢንዱስትሪዎችን ከፍቶ የስራ እድል ለመፍጠር ኃይል ያስፈልጋል ለዚህም የውሃ ሃብታችንን ለመቀጠም ግድቦችን የመገንባቱ ስራም እንደሚቀጥል እንዲሁ።
የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከመደገፍ ይልቅ የውሃ ሀብቷን መጠቀሟን ለተለያየ ዓላማ በአሉታዊ መንገድ የሚያራግቡ ጥቂት ሀገራት የያዙት መንገድ አይጠቅማቸውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት እንደሚሆን አንስተው ሌሎች ሀገራትም በቀጣይ ጥቅሙን በመረዳት ይከተሉታል ብለን እናስባለን ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት ሶስት ዓመታት 18 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን የተከለች ሲሆን በዚህ ዓመት እየተከናወነ ባለው አራተኛው ዙር መርሃ ግብርም ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጣናዊ እንዲሆን እየሰራች መሆኗ ይታወቃል።