በክረምት የእረፍት ጊዜያችን በተወከልንባቸው አካባቢዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትብብርና ተሳትፎ በማድረግ ህዝብን ለማገልገል ተዘጋጅተናል- የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በክረምት የእረፍት ጊዜያችን በተወከልንባቸው አካባቢዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትብብርና ተሳትፎ በማድረግ ህዝብን ለማገልገል ተዘጋጅተናል- የምክር ቤት አባላት
ሰኔ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ)በክረምት የእረፍት ጊዜያቸው በተወከሉባቸው አካባቢዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትብብርና ተሳትፎ በማድረግ ህዝብን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት የአረንጓዴ አሻራቸውን በቢሾፍቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ግቢ አኑረዋል።
የምክር ቤቱ አባላት መጭውን የክረምት ወቅት ለአረንጓዴ ልማት የድርሻቸውን አስተዋፅኦ ከማበርከት በተጨማሪ በተወከሉባቸው አካባቢዎች ሕዝብን ያሳተፈ ስራ ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እና ማህበራዊ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው፤ በክረምቱ የእረፍት ጊዜያቸው እነዚህ ችግሮች እንዲቃለሉ ከአስተዳደሩ ሃላፊዎችና ህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለመስራት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በእረፍት ጊዜያት ችግሮችን ማቃለል በሚቻባቸው ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና፤ ህዝብን ማወያየት እንዲሁም ችግኝ ተከላን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ወይንሸት ዘሪሁን፤ የምክር ቤቱ አባላት ዕቅድ በማውጣት ህዝብ እና ባለሀብቶችን በማስተባበር የአቅመ ደካሞችን ቤቶችን ለማደስ ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በከተማዋ ያሉ ውስብስብ ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባል አቶ ግዛቸው አይካ፤ በክረምቱ በጓሮ አትክልት ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በቤት ማደስና መሰል ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።