በጥንቃቄ ጉድለት የተያዘ ቤንዚን በፈጠረው የእሳት አደጋ የስምንት ዓመት ታዳጊ ሕይወት አለፈ

ሰኔ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በከፋ ዞን ሺሺንዳ ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ቤንዚን በጥንቃቄ ጉድለት በፈጠረው የእሳት አደጋ የስምንት ዓመት ታዳጊ ሕይወት ማለፉን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በከተማዋ መሐል ከተማ ቀጠና ልዩ ስሙ መሳለሚያ ሰፈር ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ከረፋዱ 5 ሰአት 30 ላይ በተነሳው የእሳት አደጋ በሰዉና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአስተዳደሩ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር አብርሃም አደመ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የእሳት አደጋዉ የተከሰተዉ የባለ ሶስት እግር ባጃጅ አሽከርካሪ በሕገ ወጥ መንገድ ቤንዚን ገዝቶ መኖሪያ ቤት ዉስጥ በማስቀመጡና በጥንቃቄ ጉድለት ከእሳት ጋር መያያዙን ቃጠሎው መከሰቱን ተናግረዋል።

በአደጋው አንድ የስምንት ዓመት ሕጻን ሕይወት ሲያልፍ በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።

አደጋው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት ፖሊስና የአካባቢው ሕብረተሰብ በመረባረብ እሳቱን ማጥፋት መቻሉንም ነው ምክትል ኢንስፔክተሩ ያስረዱት።

በንብረት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን እንዳልታወቀ ጠቅሰው የጉዳቱ መጠንና የአደጋው መንስኤ ላይ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የቤንዚን እጥረት መኖሩን ተከትሎ በሕገ ወጥ መንገድ ሽያጭ የሚያከናዉኑ ግለሰቦች እንዳሉ የገለጹት አዛዡ ቤንዚን በቀላሉ የእሳት አደጋ የሚፈጥር በመሆኑ መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ ሕብረተሰቡ በሕገ ወጥ መንገድ ቤንዚን ገዝቶ ከማስቀመጥ እንዲቆጠብ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም