ቀጥታ፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተመሠረተ

ሚዛን አማን፣ ሰኔ 29/2014 (ኢዜአ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መመስረቱ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሚዛን አማን ከተማ ባካሄደው የምስረታ መርሐ ግብር የክልሉን ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤን የሚመሩ የቦርድና ሥራ አስፈጻሚዎችን ሰይሟል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በምስረታ ወቅት እንዳሉት የተመሠረተው ጉባኤ የክልሉ ሰላም ተጠብቆ እንዲቆይና ለሌሎች አርዓያ መሆን እንዲችል መስራት አለበት።

በህዝቦች መካከል ሰላም፣ አንድነትና መቻቻል እንዲኖር ማድረግ የጉባኤው ዋና ዓላማ በመሆኑ እስካሁን የነበረውን አብሮነት ለማጠናከር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

በየእምነት ተቋማት ስር የሚገኙ አማኞች ከንግግር ባለፈ በተግባር የይቅርታና የሰላም ሰው መሆን እንዳለባቸው ዋና ፀሐፊው ጠቁመዋል።

እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል ሊፈጠሩ የሚችሉ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታት በጋራ የመኖር እሳቤን በምዕመናን ላይ ማስረፅ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

ህብረተሰቡን በሃይማኖት ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶችን በጋራ ቆመን የምንታገልበት ወቅት ላይ እንገኛለን ነው ያሉት ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ።

በእምነት ቢለያይ እንኳን በርካታ አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮችና የተጋመድንበትን ኢትዮጵያዊ መልካም እሴት ይበልጥ ለማጠናከር የሃይማኖት አባቶች ማስተማር አለባቸው ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሃይማኖት ጉባኤ ሰብሳቢ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የካፋ እና ሸካ፣ ቤንች ሸኮ እና ምዕራብ ኦሞ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤል ሆነው ተመርጠዋል።

የሥራ አስፈጻሚ አባላቱ ከየእምነት ተቋማት የተወከሉ ሲሆን ሼህ ሁሴን ሀሰን ምክትል ሰብሳቢ ፤ ፓስተር አባተ አለማየሁ ዋና ፀሐፊ በመሆን፤ ሌሎች አራት የእምነት ተቋማት መሪዎች በጉባኤው የሥራ ድርሻ ተሰጥቷቸው የምስረታ መርሐ ግብሩ መጠናቀቁ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም