የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የዘላቂ ልማት መሰረት በመሆኑ ኀብረተሰቡ ለስኬቱ ሊረባረብ ይገባል- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የዘላቂ ልማት መሰረት በመሆኑ ኀብረተሰቡ ለስኬቱ ሊረባረብ ይገባል- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት
ሰኔ 29/2014/ኢዜአ/ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የዘላቂ ልማት መሰረት በመሆኑ ኀብረተሰቡ ለስኬቱ መረባረብ እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
አራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 'አሻራችን ለትውልዳችን' በሚል መሪ ሀሳብ በመላ ሀገሪቷ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት በቢሾፍቱ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ግቢ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቡዜና አልቃድር፤ የምክር ቤቱ አባላት ሰራዊቱ የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር እያደረገ ላለው ተጋድሎ ከበሬታና አድናቆት ለመስጠት እዚህ ተገኝተናል ብለዋል።
በአየር ኃይል ግቢ በመገኘት አሻራችንን በማኖራችንም ታላቅ ደስታ ይሰማናል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የአረንጓዴ አሻራቸውን ከማሳረፍ ባሻገር በግቢው ውስጥ አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ህንጻ ለማደስ መረከባቸውንም ነው ያነሱት፡፡
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ውስጥ መሆኗን ገልጸው ከዚህ አኳያ ሁላችንም ለአረንጓዴ ልማት በትኩረት መስራት አለብን ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአንድ እጁ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየተዋጋ በሌላ እጁ ችግኝ እየተከለ ለትውልድ የሚሻገር አሻራውን እያኖረ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል የህዝብ ድጋፍ ያለው መሆኑን የገለጹት ሌተናል ጄነራሉ፤ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላትም በአየር ኃይል ግቢ በመገኘት ላደረጉት መልካም ተግባር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ሃይል ለአገር ሉአላዊነትና የህዝቦችን ሰላም ለማስከበር ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላት ችግኝ መትከል ለኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግብ መሰረት በመሆኑ ለመርሐግብሩ ስኬት ህብረተሰቡ በጋራ መረባረብ እንዳለበት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ግቢ ተገኝተው ለትውልድ የሚተርፍ አረንጓዴ አሻራ በማንበራቸውም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡