የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉም በዋናነት ኤጀንሲው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በግንቦት 2020 በአፋርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጨቅላ ህጻናት ህክምና አገልግሎትን ለመደገፍ የያዘው ፕሮጀክት አካል መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ድጋፉም በዋናነት ለህክምና አገልግሎት የሚውሉ ሞተር ሳይክሎች እንዲሁም የማዋለጃ አልጋዎችን ጨምሮ 33 አይነት የህክምና ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የኮሪያ አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ ሱንግሂ ቾ እንዳሉት፤ ኤጀንሲው የኢትዮጵያ መንግስት የጨቅላ ህጻናትንና እናቶችን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲው በአሁኑ ወቅት በተለይ በአፋርና ቤኒሻንጉል ክልሎች የህጻናትና እናቶች ጤናን ለማሻሻል እየተደረገ ያለውን ጥረት እየደገፈ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡
በዚህም በሁለቱ ክልሎች ለሚሰሩ ከአንድ መቶ በላይ ለሚሆኑ አዋላጅ ሃኪሞች፣ ከ600 በላይ ለሚሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ስልጠና መስጠቱን ለአብነት እንስተዋል፡፡
ኤጀንሲው በቀጣይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት፡፡
ድጋፉን የተቀበሉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ የጨቅላ ህጻናትን ሞት መቀነስ የጤናው ዘርፍ ዋነኛ ትኩረት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ድጋፉ የጤናው ዘርፍ ማነቆ የሆነውን የተደራሽነት ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ድጋፉ በተለይ በሁለቱም ክልሎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2019 ከሚወለዱ አንድ ሺህ ጨቅላ ህጻናት መካከል የነበረውን የ33 ህጻናት ሞት ምጣኔ በ2025 ወደ 21 ዝቅ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡