ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ታጠናክራለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ታጠናክራለች
ሰኔ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ይበልጥ እንደምታጠናክር በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ገለጹ።
አምባሳደሩ ይህን ያሉት 11ኛውን የደቡብ ሱዳን የነጻነት ቀን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
ወቅቱ ሁለቱ ሃገራት ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸው ከዚህ በተጨማሪም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማሳደጉ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም መግለጻቸውን ሱዳን ፖስት ዘግቧል።
የደቡብ ሱዳንን ከፍተኛ የሃይል ፍላጎትና አቅርቦትን ማሻሻልን ጨምሮ ሁለቱ እህትማማች ሃገሮች ለጋራ ብልጽግና እንደሚሰሩም አምባሳደሩ አስረድተዋል።
በሁለቱ ሃገራት መካከል ከጥቂት ወራት በፊት የተፈረመው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ስምምነት ለዚህ አንዱ ማሳያ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ነቢል በሌሎች ዘርፎችም ላይ ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ለደቡብ ሱዳን የ100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።
በዚህ ስምምነት መሰረትም የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን እስከ 400 ሜጋ ዋት ለማድረስ የታሰበ ሲሆን ለዚሁ አገልግሎት የሚሆኑ መሰረተ ልማቶች በሁለቱ ሃገራት እየተገነቡ መሆኑም ይታወቃል።
የዚህ ዓይነቱ የሃይል አቅርቦት ስምምነት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እድገትን በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።